ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለኦማን መንግስት የሃዘን መግለጫ መልዕክት ላኩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለኦማን መንግስት የሃዘን መግለጫ መልዕክት ላኩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2012 (ኢዜአ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኦማን ሱልጣን ህልፈት ማዘናቸውን የሚገልጽ መልዕክት ለአገሪቱ መንግስት ላኩ።
ፕሬዚዳንቷና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦማን ሱልጣኔት ንጉስ ሱልጣን ቃቦስ ቢን ሳይድ ቢን ታይሙር ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹበትን የጽሁፍ መልዕክት ለአገሪቱ መንግስት ልከዋል።
መልዕክቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ አምባሳደር ሞሐመድ ድሪር በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዛሬ በመገኘት ለሚኒስትሩ ዩሱፍ ቢን አለዊ ቢን አብዱላህ አቅርበዋል።
መሪዎቹ በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለንጉሱ ቤተሰብና ለመላው የኦማን ህዝብ መጽናናትን እንደሚመኝ ገልጸዋል።
የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቢን አለዊ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በኩል ለቀረበው የሐዘን መልዕክት አመስግነው፤ መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።