በትግራይ ምእራብ ዞን 360 ሰዎች በተደረገላቸው ሕክምና የዓይን ብርሃናቸው ተመለሰ

45
ሁመራ ጥር 10/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ምእራብ ዞን በዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቅተው የነበሩ 360 ሰዎች በተደረገላቸው ሕክምና የዓይን ብርሃናቸው መመለሱን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ። የሕሙማኑ የዓይን ብርሃን የተመለሰው መምሪያው ከትግራይ ክልል ጤና ቢሮና ሂማንታሪያን ካታሪክት ከተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ባደረጉት ነጻ የህክምና አገልግሎት ነው። በካህሳይ አበራ ሆስፒታል ላለፉት ስምንት ቀናት በተሰጠው አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ የዓይን ስፔሻሊስት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም በትራኮማ በሽታ ተጠቅተው የቆዩ 51 ሰዎችም የነጻ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ  መሆናቸውን መምሪያ ገልጿል። በዓይን ሞራግርዶሽ ምክንያት የሁለቱን ዓይኖቻቸውን ብርሃን ከሁለት ወራት እንዳጡ የተናገሩት የቃፍታ ሁመራ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ እርጥብነሽ ገብረዮሃንስ በተሰጣቸው አገልግሎት ብርሃናቸው እንደተመለሳቸው ተናግረዋል። በአገልግሎቱ ከተጠቀሙት ቤተሰቦች አንዱ አቶ ማማይ አባተ ናቸው። የወልቃይት ወረዳ ነዋሪው አቶ ማማይ ልጃቸው በትራኮማ በሽታ ስትሰቃይ እንደነበረችና የቀለም ጽሁፍ ለመለየት ስትቸገር እንደነበር ያወሳሉ። ሰሞኑን በተደረገላት ሕክምና ከሕመሟ መፈወሷንና ማንበብና ቀለማትን መለየት እንደቻለች ገልጸዋል። የሂማንተሪያን ካታራክት የበጎ አድራጊ ፕሮጀክት ከሕክምናው በተጨማሪ  የህሙማኑን ቁርስና ምሳ ወጪ መሸፈኑን የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ባለሙያ አቶ አብርሃ  ደስታ ናቸው። በአገልግሎቱ ከአንድ ሺህ በላይ ታካሚዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፤ 411ዱ አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በክልሉ ለ15 ዓመታት በሰጠው ነጻ የዓይን ህክምና አገልግሎት ከ40 ሺህ በላይ ሕሙማንን ተጠቃሚ ማድረጉን በክልሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተስፋይ ተስፋማሪያም  አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም