ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት የፖለቲካ ገለልተኝነቱን ጠብቆ ለአገር ህልውና ዘብ መቆም አለበት... ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

አዲስ አበባ፤  ጥር 10/2012 (ኢዜአ)  የአገር መከላከያ ሰራዊት የፖለቲካ ገለልተኝነቱን ጠብቆ ለአገር ህልውና ዘብ የመቆሙን ኃላፊነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ፍሬያማ የለውጥ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል። ለ65 ከፍተኛ የአገር መከላከያ ሰራዊት መኮንኖች የማእረግ ሹመት ተሰጥቷል። በተሰጠው የማእረግ ሹመት ስድስቱ ከሜጄር ጄኔራልነት ወደሌተናል ጄኔራል፣ 19ኙ ከብርጋዴር ጄኔራል ወደሜጄር ጄኔራል፣ እንዲሁም 40ዎቹ ከኮሎኔል ወደ ብርጋዴር ጄኔራልነት አድገዋል። የማእረግ ሹመት ካገኙት መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ በዚህን ወቅት ባስተላለፉት መልእክት "የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊነት ምልክቱ ጀግንነት ደግሞ ተግባሩ ነው" ብለዋል። ሰራዊቱ የአገር አጥር ሆኖ ከማገልገሉም በተጨማሪ የአርሶ አደሩ ማሳ ድረስ እየዘለቀ የልማት አለኝታነቱን ማሳየቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሰራዊቱን ለማዘመንና ክብሩና ተልዕኮውን በሚመጥን መልኩ ለማደራጀት የለውጥ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ስራው ከወዲሁ ውጤት ማስመዝገብ መጀመሩን ገልጸዋል። በለውጥ ስራው የአዋጅ ማሻሻያዎቸን ጨምሮ የማዕረግ፣ የደመወዝና የደንብ ልብስ ጉዳዮች ምላሽ ማግኘታቸውን አብራርተዋል። ሰራዊቱም ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቁን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። ማንኛውም ኃይል ከአገር ህልውና እንደማይበልጥ ገልጸው፤ ''ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ህግና ስርዓትን አክብረው የመንቀሳቀስ ግዴታና ኃላፊነት አለባቸው'' ብለዋል። መከላከያ ሰራዊቱ ከማናቸውም የፖለቲካ ኃይሎች ገለልተኛ ሆኖ የአገርን ሰላምና ሉአላዊነት እንዲያስጠብቅ አሳስበዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ "ሰራዊቱ ከየትኛውም ብሔር ይወለድ ከየትም አካባቢ ይምጣ የመከላከያ አባል አስከሆነ ድረስ የኢትዮጵያ ሃብት ነው" ብለዋል። በለውጡ ሰራዊቱ 'እኔ የህዝብ ነኝ' የሚል አመለካካት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የተሳካ ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል። የመከላከያ ሰራዊት ስትራቴጂስት መሪ እንዲኖረው የሚያግዙ ተጨማሪ አዳዲስ ኮሌጆች መከፈታቸውም የለውጥ ስራው አካል መሆኑን የተናገሩት አቶ ለማ፤ የመከላከያ ዲፕሎማሲን በመጠቀም በተለይ በአቅም ግንባታ ዘርፍ ከወዳጅ አገሮች ጋር ፍሬያማ ትብብር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊቱ ማናቸውንም ግዳጅ ለመፈጸም ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም