ኢትዮጰያዊ አንድነትና መከባበር እንዲጎለብት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጰያዊ አንድነትና መከባበር እንዲጎለብት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ተባለ
(ኢዜአ) ጥር 9 / 2012 ኢትዮጰያዊ አንድነትና መከባበር እንዲጎለብት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አትናቴዎስ አሳሰቡ ። ሊቀ ጳጳሱ የጥምቀት በዓልን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የህዝቡን የጥንት የአብሮነትና የአንድነት እሴት እየተሸረሸረ መጥቷል። በዚህም አንዱ አንዱን ከማክበር ይልቅ ፀብ አጫሪነት እየተስፋፋና እርስ በእርስ ወደ አለመተማመን ደረጃ እየተደረሰ ነው ብለዋል ። ሀገሪቱን ከዚህ ችግር ለመታደግም የበፊቱን አንድነት፣ ፍቅር፣ መከባበርና መቻቻል ለመመለስ ሁሉም በየእምነቱ መረባረብና ማስተማር እንዳለበት አሳስበዋል ። በተለይም የተለያዩ በዓላትን በጋራ በማክበር በየትኛውም የእምነት ተቋም ላይ የጥፋት እጁን የሚያነሳ አካል የሁሉም ጠላት በመሆኑ በጋራ ማስተማርና መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል። መንግስትም በብሔርና በሐይማኖት እየከፋፈሉ ህብረተሰቡን እርስ በእርስ የሚያጋጩ ሃይሎችን በመለየት አስተማሪ እርምጃ መውሰድና እየላላ የመጣውን የህግ የበላይነት ማስከበር እንዳለበት ገልፀዋል። የኢትዮጵያ የበፊት አባቶች ቤተ ክርስቲያንና መስጅድ በጋራ ሲገነቡ እንጂ ሲያቃጥሉ አላየንም ያሉት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ መከባበርንና አንድነትን እንጅ ጥቃትና በደልን በየትኛውም ሐይማኖት እንደማይፈቅድ ገልጸዋል፡፡ አሁንም የጥምቀትን በዓል ስናከብር እንደ ቀድሞው አባቶቻችን በአንድነት፣ በሰላምና በፍቅር እንዲሆን ምዕምናኑ፣ ወጣቱና ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ በተለይ "ክርስትናና እስልምና ጥብቅ ትስስር እንዳለቻው የገለጹት አቡነ አትናቴወስ ሊለያዩን ለሚሞክሩ ጥቅመኞች በር ሳንከፍት አንድነታችንን ማጠናከር አለብን" ብለዋል፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው በዓሉ የሰላም፣፤ የፍቅርና የአብሮነት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡ የጥምቀት በዓልን በሰላማዊ መንገድ ለማክበር ተገቢው ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የደሴ ከተማ የአስተዳደርና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አበራ አሉላ ናቸው። የከተማው ነዋሪዎች፣የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ባለ ድርሻ አካላት በማስተባበርም የስጋት አካባቢዎችን በመለየት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። የሰላም፣ የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነው የወሎና አካባቢው ህዝብ የቀደመ መልካም እሴቶችን በመጠበቅ ለበዓሉ ሰላም መሆን የድርሻቸውን እንደሚወጣም ተናግሯል። የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኤርሚያስ መሃመድ በበኩሉ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን ተደራጅተው ሰላም ለማስከበር መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።