መቐለ ሰብዓ እንደርታ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግን እየመራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መቐለ ሰብዓ እንደርታ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግን እየመራ ነው
አዲስ አበባ ጥር 9 / 2012 (ኢዜአ) መቐለ ሰብዓ እንደርታ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግን እየመራ ነው። በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በክልል ከተሞች ተካሄደዋል። ጎንደር ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጎንደር ከተማን 30 ለ 24 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ውጤቱንም ተከትሎ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል። በአንጻሩ ጎንደር ከተማ በሊጉ ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ጨዋታው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መካሄዱንና በስፖርታዊ ጨዋነት ደረጃ የሚያመሰግን ነገር የታየበት ነው ብለዋል። የመቐለ ሰብዓ እንደርታ የእጅ ኳስ ክለብ ልዑካን ቡድን ጎንደር ከተማ ሲገባ የተጋጣሚው ቡድን ልዑካን ደማቅ አቀባባል እንዳረገለት ገልጸዋል። ከጨዋታው በተጨማሪ ልዑካን ቡድኑ በጎንደር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችንም መጎብኘቱን ተናግረዋል። አቶ ሞላ የጎንደር ከተማ የቡድን መሪ አቶ ደመላሽ መካሻውና የጎንደር ከተማ ወጣቶች ላከናወኑት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እንደዚህ አይነት መሰል ተግባራት በሌሎች የእጅ ኳስ ክለቦች ዘንድም ሊታይ እንደሚገባም አሳስበዋል። ቡታጅራ ላይ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ቡታጅራ ከተማን 25 ለ 20 በማሸነፍ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የውደድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከሚዛን አማን ከተማ ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት፤ መከላከያ ከከምባታ ዱራሜ ከረፋዱ 4 ሠዓት ከ30 እንዲሁም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ ከረፋዱ 5 ሠዓት ከ30 ይጫወታሉ። በሌላ የስፖርት ዜና በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ መከላከያን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 አሸንፏል። ነገም ቀሪ የሳምንቱ መርሃ ግብሮች በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ሙገር ሲሚንቶ ከወላይታ ድቻ ሙገር ላይ ከረፋዱ 4፡00 ሠዓት የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ፖሊስ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ይጫወታሉ።