ቀጥታ፡

የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ይፈልጋሉ

አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ለመሠማራት ፍላጎት እንዳላቸው የአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየው የአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ከ60 በላይ የሚሆኑ የአሜሪካ ኩባንያ ተወካዮች በምክትል ንግድ ሚኒስትሩ መሪነት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረግ ጀምረዋል። ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላንን በውይይቱ እንደተናገሩት፤ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት አላቸው። ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለቤት የሆነችና ተከታታይ እድገት ያስመዘገበች አገር መሆኗን ገልጸው አጋርነቱ አሁን ካለበት ደረጃ ማደግ አለበት ብለዋል። የአሁኑ ጉብኝት የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመነት ተሳታፊ እንዲሆኑ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸውና በቀጣይም እንዲህ ያለው ጥረት ይጠናከራል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የጀመረውን የማሻሻያ እርምጃ የአሜሪካ መንግሥት እንደሚደግፍ ጠቁመው በመስቀል አደባባይ የደረሰውን ጥቃት አሜሪካ ታወግዛለች ብለዋል። የተፈጸመውን ጥቃትም ለማጣራት የሚያግዝ ከአሜሪካ ኤፍ ቢ አይ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ እንዳሰበችም ፍንጭ ሰጥተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ በበኩላቸው፤ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት በምጣኔ ኃብትም ረገድ ሊሰፋ ይገባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያም አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት፤ እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ያላት አገር በመሆኗ የአሜሪካ ኩባንያዎች ተመራጭ ያደርጓቷል ብለዋል። በሁለቱ አገራት መከካል ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን በመስቀል አደባባይ የደረሰውን ጥቃት ለማጣራት የሚያስችል የኤፍ ቢ አይ ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ፍንጭ የሰጡ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ስለ ጉዳዩ የተባለ ነገር የለም።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም