የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ለ21ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 500 ምልምል ፖሊሶች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ለ21ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 500 ምልምል ፖሊሶች አስመረቀ
(ኢዜአ) ጥር 9 / 2012 የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ለ21ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 500 ምልምል ፖሊሶች አስመረቀ። የከተማዋን ደህንነት ለማጠናከርና መጪውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ማድረግ እንዲቻል የፖሊስ ኃይሉን አቅም ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ በዚሁ ወቅት አስታውቋል። በኮልፌ ፖሊስ አካዳሚ ሰልጥነው በዛሬው እለት ለምረቃ የበቁት የፖሊስ አባላቱ ሁሉን አቀፍና አካቶ የወንጀል መከላከል ክህሎት እንዲያካብቱ የተደረገ በመሆኑ ከከዚህ ቀደሞቹ የተለየ ያደርጋቸዋል ተብሏል። ስልጠናው መስማት የተሳናቸውን ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ አገልገሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተመልክቷል። በምረቃው ስነ-ስርዓቱ ላይ የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተመራቂዎቹ ከራስ ጥቅም ይልቅ የህዝብ ጥቅምን በማስቀድም በፍፁም ታማኝነት ማህበረሰቡን በማገልገል ሙያዊ ግዴታውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ፖሊስ ወንጀልን ቀድሞ በመካላከል፣ ከተፈጸመም ተጠያቂዎቹን ተከታትሎ ህግ ፊት በማቅረብ፣ ለተበደሉት ደራሽ የሆነ የሙያ ባለቤት በመሆኑ “ልቡ ሩህሩህ፣ አዕምሮው ብሩህ፤ እጁ ንጹህ” ሊሆን እንደሚገባም መክረዋል። የኮልፌ ፖሊስ አካዳሚ ዳይሬክተ ረዳት ኮሚሽነር መኮንን አሻግሬ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ ሁሉን አቀፍና አካቶ የወንጀል መከላከልን መሰረት ያደረገ ስልጠና እንደተሰጣቸው ጠቅሰው ይህም ከበፊቶቹ ሰልጣኞች የተለየያደርጋቸዋል ብለዋል። ሰልጣኞቹ መስማት በተሳናቸው ዜጎች የሚፈጸሙ ወንጀልተግባራትን ለመከላከል ሲባል ተግባር ተኮር የምልክት ቋንቋ በስርዓተ ትምህርቱ ተካትቶ መሰጠቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትህና ፀጥታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ግዛው ለኢዜአ እንደነገሩት ከተማው ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል እንዲኖረው መደረጉ የከተማዋን ሰላም፣ ደህንነትና ጸጥታ የበለጠ ለማጠናከር አበርክቶ አለው። አቶ ኤፍሬም አክለውም የከተማውን ሰላምና ፀጥታ የበለጠ ለማስጠበቅ ብሎም መጪው አገራዊ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ የፖሊስ ሃይሉን በሰው ኃይልና ግብዓት ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ አድማ ብተናንና ፖሊሳዊ የአካል ብቃትን የሚያሳዩ ትርኢቶች በተመራቂዎቹ ቀርበዋል። አካዳሚው ለከተማ አስተዳደሩ የፖሊስ ሃይል አበርክቶ ለነበራቸው ተቋማትና ግለሰቦች እንዲሁም የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ አሰልጣኞችና ተመራቂዎች የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የሰርተፊኬት ሽልማት ሰጧል። አካዳሚው ፖሊሳዊ ስልጠና መስጠት ከጀመረ 16 ዓመታት የሆነው ሲሆን አሰልጥኖ ሲያስመርቅም የዛሬው 21ኛው ዙር ነው ተብሏል።