ከጋሞ አባቶች ይቅር ባይነትንና መቻቻልን መማር ይገባል

113

ጎንደር፤  ጥር 9/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከጋሞ አባቶችና ወጣቶች መላው የሀገሪቱ ህዝቦች ፍቅርን፣ ይቅርታንና መቻቻልን መማር ይገባል ሲሉ የጎንደር ከተማ የሃገር ሽማግሌዎች ገለፁ።

የጋሞ አባቶችና ወጣቶች የሰላምና አንድነት ጉዞ አባላት ጎንደር ከተማ ሲደርሱ ደማቅና የጀግና አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

የጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሀይሉ ታደሰ በአቀባበሉ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የጋሞ አባቶችና ወጣቶች ለእውነትኛ ፍቅርና አንድነት የቆሙ ናቸው።

በመላ ሃገሪቱ አንድነት፣ መቻቻልና መተሳሰብ እየቀነሰ መጥቷል ያሉት የሃገር ሽማግሌው ከጋሞ አባቶችና ወጣቶች ስለ አብሮ መኖር መማር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉና የህዝቦችን አንድነት በመመለስ ለሀገር ግንባታ፣ ሰላምና ብልፅግና አብረን እንሰራለንም ብለዋል።

በተለይም ሀገሪቱ የህብረ-ብሄራዊ አንድነት ማሳያ ትሆን ዘንድም የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱን ህዝቦች አንድነትና መተሳሰብ የሚሸረሽሩ አመለካከቶችንና ተግባሮችን ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ሆነው እንደሚታገሉም ጠቁመዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በመምህርነት ለ40 አመታት ያገለገሉትና የጋሞ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑት መምህር ወልዴ መና በበኩላቸው የህዝቦች አብሮነትና መተባበር የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ያደርጋል።

"ከጋሞ አባቶችና ወጣቶች ብዙ ልምድና ተሞክሮ እንወስዳለን" ያሉት ደግሞ የጎንደር ሰላም፣ ልማትና ሸንጎ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ባዩ በዛብህ ናቸው፡፡

ልምዳቸውን ሊያካፍሉ የመጡት የጋሞ አባቶችና ወጣቶችም በጎንደር በሚከበረውና በርካታ ህዝብ በሚታደመው የጥምቀት በዓል ሰሞን በመሆኑ የሰላም ተልእኮአቸውን ግብ እንዲመታ በማድረግ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የጋሞ አባቶችና ወጣቶች የሰላምና አንድነት ጉዞ አባላት አስተባባሪ የሆነው ወጣት ሙሉቀን ወልቃ በበኩሉ  የዚህ ጉዞ አላማ ስህተትን በስህተት ሳይሆን በይቅርታ ለመፍታትና ለማረም የሚያስችል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ነው፡፡

የጋሞ አባቶች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በቀልን ለማሰቀረት ያደረጉትን ተማፅኖ የጋሞ ወጣትም የአባቶችን ትእዛዝ የተቀበለ መሆኑን ያስታወሰው ወጣቱ ሁሉም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሰላምና ለልማት በጋራ መስራት እንዳለባቸው መክሯል፡፡

የጉዞው አባላት በጎንደር የጥምቀትን በዓል በክብር እንግድነት የሚታደሙ ሲሆን በቀጣይ ጥር 13 ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የጋራ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም