ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፖርት ማህበራዊ ልማትና ሁለንተናዊ እድገት በሚያረጋግጥ መልኩ መቃኘት አለበት ተባለ

ጥር 9 /2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፖርት የማህበራዊ ልማትና ሁለንተናዊ አገራዊ እድገት በሚያረጋግጥ መልኩ ሊቃኝ እንደሚገባ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ገለፀ ። የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ያዘጋጀው የአገሪቱ  ስፖርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሪፎርም የተመለከተ  ውይይት በመቀለ ተካሔዷል ። የስፖርት ዘርፉ ከግለሰቦች እጅ ወጥቶ በህብረተሰብ ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባው በውይይቱ ላይ የቀረበ  አንድ ጥናት አመለከተ። የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን በአገሪቱ ስፖርት ፖሊሲና ስትራተጂ ሪፎርም ዙሪያ በትግራይ ክልል  ከ53 ወረዳዎች ከተውጣጡ የስፖርት አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊና የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደተናገሩት የስፖርት ፖሊሲና ስትራተጂ ሪፎርም በመካሄድ ላይ ነው ። የሪፎርሙ ዋና አላማ ዜጎች በአካላዊ ብቃትና በአእምሮአዊ ብልፅግና የተላበሱ ለማድረግ ነው። በስፖርቱ ዘርፍ በጥናት የተደገፈ ሪፎርም መደረጉ እስከ አሁን አየተመዘገበ ከመጣው ውጤት በላይ ለማስመዝገብ ይረዳል ብለዋል ። የሪፎርም ጥናቱን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ሳሙኤል ስለሺ “የኢትዮጵያ ስፖርት ልማት ወቅታዊ ሁኔታ እና የወደፊት አቅጣጫ” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ስፖርት ማህበራዊ ልማትና ሁለንተናዊ እድገት እንዲያረጋግጥ የአለም አቀፍ የስፖርት ልማት መለኪያዎችን ማሟላት እንዳለበትም በፅሁፋቸው አመላክተዋል ። '' በስፖርት ፖሊሲ ትግበራ ፣በሰው ሃብት ልማት፣ በፋይናንስ አቅርቦትና በማዘውተሪያ ቦታዎች ልማት ላይ ያሉትን ክፍተቶች ሊፈተሹ ይገባል'' ብለዋል። የአገሪቱ ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ከግለሰቦች እጅ ወጥቶ የህብረተሰብ ተሳትፎ ማካተት እንደሚገባውም ጥናት አቅራቢው ተናግረዋል። የትግራይ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ በበኩላቸው ስፖርት የአንድ አገር ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ መመራት አለበት ብለዋል። ስፖርት ከመዝናኛ በተጨማሪ የህዝብ ሁለንተናው እድገት ማረጋገጥ የሚችል ዘርፍ መሆኑ እንደሚገባው አስገንዝበዋል ። እስካሁን ባለው የአገርቱ የስፖርት እንቅስቃሴ የህዝብ መሰረት ይዞ የህዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኝነት በሚያረጋግጥ መልኩ እየተመራ እንዳልሆነም ተናግረዋል። የስፖርት ፖሊሲ በዘርፉ ያመጣቸው ለውጦች እንዳሉ ሆነው ዛሬ ለውይይት የቀረበው ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ ስፖርት አንዱ የአገር ልማት ማረጋገጫ እንዲሆን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። በተለይ በስፖርታዊ ጨዋነት የሚታዩ የስነ ምግባር ጉድለቶች ዘርፉ ወደኋላ እንዳይመልሰው የሚያሰጋ መሆኑን የቢሮ ሀላፊዋ ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት መካከል በጋንታ አፈሹም ወረዳ የስፖርት አስተባባሪ መምህር ገብረመድህን ገብረመስቀል እንዳሉት የውይይት መድረኩ በስፖርት ዘርፉ አቅም የሚሆንና ሊያሰራ የሚችል ነው ብለዋል። በትግራይ አሁን ካለው የስፖርት መነቃቃት አንፃር የቀረበው የሪፎርም ጥናት የክልሉ ስፖርት ወደፊት ሊያራምደው ይችላል የሚል ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል ። በውይይት መድረኩ ላይ ከ300 በላይ የሚሆኑየዞንና የወረዳ  የስፖርት አመራሮች፣ከትምህርት ፅህፈት ቤት የተወከሉ ባለሙያዎችና የወረዳ ስፖርት አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም