የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ቀድሞም አንድ ናቸው - ትውልደ ኤርትራዊ ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ቀድሞም አንድ ናቸው - ትውልደ ኤርትራዊ ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብር

አዲስ አበባ፤ ጥር 9 /2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ቀድሞም ሆነ አሁን አንድ ናቸው ሲል ትውልደ ኤርትራዊው ስዊድናዊ ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብር ተናገረ።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ደግሞ ኢትዮጵያና ኤርትራ በቦክስ ስፖርት ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ስራዎችን ለመከወን እየተዘጋጁ እንደሆነ ገልጿል። እ.አ.አ 2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው ኦሎምፒክ አፍሪካን በቦክስ ውድድር የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት ከየካቲት 12-21 ቀን 2012 ዓ.ም በሴኔጋል የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል።
በውድድሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞችን ለመምረጥም ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም የማጣሪያ ውድድር ተካሂዷል።
ከማጣሪያ ውድድሩ በተጨማሪ በ63 ኪሎ ግራም ወንድ በትውልድ ኤርትራዊ በዜግነት ስዊድናዊ የሆነው ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብርና ኢትዮጵያዊው ካሳሁን ኃይሉ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው ካሳሁን ተጋጣሚውን በነጥብ አሸንፎታል።
ኢዜአ የ27 ዓመቱን ትውልደ ኤርትራዊ የስዊድን ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብርን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መጫወቱ የፈጠረበትን ስሜት እንዲሁም ስለ ቦክስ ሕይወቱ አነጋግሮታል።
ቢኒያም ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የቻለው ዳኛቸው ዘርጋ ከሚባል የፌስቡክ ጓደኛው ጋር በመጻጻፍ እንደሆነና ዳኛቸው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን በማነጋገር ዕድሉን እንዳመቻቸለት ገልጿል።
በአሁኑ የፌዴራል ፖሊስ የቦክስ ክለብ በድሮ ስያሜው /ኦሜድላ/ ሜዳ ለጨዋታው ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየም ተናግሯል።
ባደረገው ጨዋታ ደስተኛ መሆኑንና የአየር ሁኔታው እንደከበደው የገለጸው ቢኒያም የኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረገለት መልካም አቀባበል ምስጋና አቅርቧል።
"እናትና አባቴ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቴን ተከትሎ ከኤርትራ ሊያዩኝ መምጣታቸውና ከቤተሰቤ ጋር መገናኘቴ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል" ብሏል ቦክሰኛ ቢኒያም።
ቢኒያም ቦክስ የጀመረው ከ12 ዓመቱ ጀምሮ እንደሆነና ለ15 ዓመት በስፖርቱ ማሳለፉንም ገልጿል።
እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ ኑሮውን በስዊድን አድርጎ ስኪልስቱና ለሚባል የቦክስ ክለብ እየተጫወተ ይገኛል።
ስዊድንን በመወከል በዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር መሳተፍ እንደቻለና እ.አ.አ 2020 ወደ ፕሮፌሽናል ቦክሰኝነት ለማደግ እቅድ እንዳለው ይናገራል።
ቢኒያም በኤርትራ አምስት የሚሆኑ የቦክስ ክለቦች ቢኖሩም ቀደም ሲል በስፖርቱ የነበረው የተነቃቃ እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ነው የተናገረው።
የዚህ ምክንያቱ የኤርትራ የቦክስ ፌዴሬሽን አገራዊና ክለባዊ ውደድሮችን እያዘጋጀ አለመሆኑ እንደሆነ ጠቁሞ ፌዴሬሽኑ በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ጠይቋል።
"የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ድሮም ቢሆን አንድ ናቸው ምንም የተለየ ነገር የለም አለመግባባቶች ነበሩ አሁን ግን መልሰው መገናኘት ጀምረዋል" ብሏል ቢኒያም ተስፋጋብር።
ከትናንቱ ጨዋታ ጥሩ የሚባል ተሞክሮ እንደወሰደና የኢትዮጵያና ኤርትራ ቦክሰኞች በተመሳሳይ ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል።
የቦክስ ስፖርት አፍቃሪው ዳኛቸው ዘርጋም ከቢኒያም ጋር በፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ጓደኛ ከሆኑ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ይገልጻል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበሩ ኤርትራዊያን ቦክሰኞች በሚነግረው ነገር ደስተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ መጥቶ እንዲጫወት ያቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉን ተናግሯል።
ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ጨዋታው መካሄዱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በቦክስ ለማጠናከር መልካም እድል የሚፈጥር እንደሆነ ታምኖበት ጨዋታው መዘጋጀቱንም ገልጿል።
'ቢኒያም ጨዋታውን ለማድረግ የመጣበት አንዱ ምክንያት ኤርትራዊያን ታዳጊ ቦክሰኞች እሱን አይተው እንዲበረታቱና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከአገሪቷ ቦክሰኞች ጋር ጨዋታ በማድረግ ልምድ እንዲያገኙ ካለው ፍላጎት አንጻር ነው' ብሏል ዳኛቸው።
ዮናስ ወልዱ፣ ቴዎፍሎስ ይስሐቅና ባስሊዮስ የሚባሉ የኤርትራ ቦክሰኞች በኢትዮጵያ ክለቦች ውስጥ ይጫወቱ እንደነበረና በአገራቱ መካከል አለመግባበት ሲፈጠር ወደ አገራቸው እንደሄዱ ያወሳል።
የቢኒያም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መጫወት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸው በስፖርትም እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ፌዴሬሽኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ ብሏል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ በበኩላቸው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተቋርጦ የቆየው ግንኙነት ዳግም መጀመሩን ምክንያት በማድረግ የአገራቱን የስፖርትና የባህል ግንኙነት ለማጠናከር ፌዴሬሽኑ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ ከኤርትራ ቦክስ ፌዴሬሽን ጋር መደበኛ የሚባል ግንኙነት መፍጠሩንና በሚያዚያ 2012 ዓ.ም አስመራ ላይ የኢትዮ-ኤርትራ የቦክስ ውድድር ለማዘጋጀት መታቀዱንም ጠቁመዋል።
በኤርትራ ላለው የቦክስ ሪንግ እጥረት መፍትሔ ይበጅ ዘንድ ኤርትራዊያን ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በመግዛት ይዘው እየሄዱ እንደሆነም እንዲሁ።
በስፖርቱ ከሚደረገው የልምድ ልውውጥ ባሻገር የባህል ልምድ ልውውጥ ለማድረግ መታሰቡንም አክለዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የቦክስ ልምድ ልውውጥ ለማድረግና የቦክሰኞቿን ልምድ ለማሳደግ ፌዴሬሽኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።