በሴኔጋል ዳካር በሚካሄደው የ2020 ኦሎምፒክ የቦክስ የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
በሴኔጋል ዳካር በሚካሄደው የ2020 ኦሎምፒክ የቦክስ የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ተለዩ

አዲስ አበባ ጥር 08/2012 (ኢዜአ) በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር በሚካሄደው የ2020 ኦሎምፒክ የቦክስ የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ታውቀዋል። እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛ ኦሎምፒክ በቦክስ ውድድር አፍሪካን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት ከየካቲት 12 እስከ 21 ቀን 2012 ዓ.ም በሴኔጋል የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል። በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ቦክሰኞችን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደ ሲሆን አምስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በ52 ኪሎ ግራም ወንድ የአዲስ አበባ ፖሊሱ ዳዊት በቀለ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶቹን ያዕቆብ በለጠን፤ በ57 ኪሎ ግራም ወንድ የአዲስ አበባ ፖሊሱ ፍቅረማርያም ያደሳ የድሬዳዋ ከተማውን አብዱልሰላም አቡበከርን በነጥብ አሸንፈዋል። በ63 ኪሎ ግራም ወንድ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶቹ አብርሃም ዓለም የፌዴራል ፖሊሱን ሳሙኤል ሙሉጌታ እንዲሁም በ69 ኪሎ ግራም ወንድ የአዲስ አበባ ፖሊሱ መስፍን ብሩ የፌዴራል ፖሊሱን ቢንያም ተስፋዬ በነጥብ ማሸነፍ ችለዋል። በ75 ኪሎ ግራም ተመስገን ምትኩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶቹን ባምላክ ደጉ በበቃኝ አሸንፎታል። አሸናፊዎቹ በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር በሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ማጣሪያ ላይ ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዛሬ ለውድድር ቀርበው የተለዩት ቦክሰኞች ባለፈው ዓመት በተካሄዱ ብሔራዊ ውድድሮችና በ2012 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው የመጀመሪያው የክለቦች ውድድር ባገኙት ውጤት መሰረት ነው። ''በዛሬው ውድድር በክፍት ሜዳ ጨዋታዎቹ መካሄዳቸው የአየር ንብረቱ ለተወዳዳሪዎቹ ትንሽ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል'' ብለዋል። የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ባደረገው ስብስባ በ81 ኪሎ ግራም ወንድ ሰይፈ ከበደ ከአዲስ አበባ ፖሊስ በ51 ኪሎ ግራም ሴት አገሬ እማኙ ከጎንደር ከተማ በቀጥታ በማጣሪያው እንዲሳተፉ መወሰኑን ገልጸዋል። ኮሚቴው ይሄን የወሰነው ተወዳዳሪዎቹ ባላቸው ወቅታዊ ብቃት በኪሎ ግራም ዘርፉ ከነሱ ጋር የሚመጣጠን ተወዳዳሪ ባለመገኘቱ እንደሆነ አመልክተዋል። በሴት አንድ ተወዳዳሪ ብቻ ያለው የቦክስ ክለቦች በቂ የሚባል ሴት ቦክሰኞች አለመኖራቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይ በሴት ቦክሰኞች ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ፌዴሬሽኑ ከክለቦች፣ ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሚመረጠው እንደ ተወዳዳሪዎቹ ሁሉ በብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር የተሻለ ውጤት ያገኘ በሚለው መመዘኛ እንደሆነ አቶ ስንታየሁ ገልጸው፤ አሰልጣኙ ነገ እንደሚመረጥ አመልክተዋል። በሴኔጋሉ የማጣሪያ ውድድር የሚሳተፉ ቦክሰኞች ከነገ በስቲያ ጀምሮ በአርባምንጭ ከተማ ለአንድ ወር የሚቆይ የዝግጅት ጊዜ እንደሚኖራቸው አክለዋል። ከማጣሪያ ውድድር በተጨማሪ በ63 ኪሎ ግራም ወንድ የኤርትራው ቦክሰኛ ቢኒያም ተስፋጋብርና ኢትዮጵያዊው ካሳሁን ሃይሉ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው ካሳሁን ተጋጣሚውን በነጥብ አሸንፎታል። ጨዋታዎቹ ከመጀመራቸው በፊት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልሰመድ መሐመድ ወደ ቦክስ ሪንግ ገብተው ያደረጉት የቦክስ ጨዋታ በስታዲየሙ የተገኘውን የስፖርቱ አፍቃሪ ያዝናና ነበር። በማጣሪያ ውድድሩና በወዳጅነት ጨዋታው ላይ ለተሳተፉ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል። የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰንና ሌሎች የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሜዳሊያዎቹን ለቦክሰኞቹ አበርክተዋል።