ከከተሞች ፈጣን እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የተደራጀ አመራር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ከከተሞች ፈጣን እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የተደራጀ አመራር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ ጥር 08/2012 (ኢዜአ ) ከአገሪቱ ከተሞች ፈጣን እድገት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከወዲሁ በአግባቡ መፍታት ይቻል ዘንድ በወጉ የተደራጀ አመራር ሊፈጠር እንደሚገባ ተገለፀ። በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በተዘጋጀው የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ የሚመክር ስብሰባ ዛሬ አዳማ ተጀምሯል። በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሄር እንደተናገሩት ከከተሞች ፈጣን እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከወዲሁ የተደራጀ አመራር መስጠት ይጠበቃል። በዚህ ረገድ መሪ እቅዱ ሃገሪቱ በዘርፉ ላለፉት አመታት ስትተገብረው የነበረውን የእቅድ አፈፃፀም ድክመትና ጥንካሬ መሰረት አድርጎ የወጣና ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ መሆኑም አንስተዋል። በተለይም የከተሞችን የቤት አቅርቦት፣የመሰረተ ልማት ግንባታ ፣የፋይናንስ አሰባሰብ፣የከተማ ፕላን ዝግጅት የአስተዳደር ስርአትንና ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የነበሩ ድክመቶችን በጥራት የገመገመ መሆኑንም እንዲሁ። “በኢትዮጵያ የከተሞች በፍጥነት ማደግ በአግባቡ ከተመራ የልማት መሰረት ሊሆን ይቻላል፤ በአግባቡ ካልተመራ ግን ለሃገር እድገትና ልማት ስጋት ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ወደ ከተማ ከሚፈልሰው የሰው ብዛት ጋር የተመጣጠነ የቤት አቅርቦት፣ የስራ ፈጠራና መሰል የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎቶች በጥራትና በስፋት ከወዲሁ እየተመለሱ ካልሄዱ በቀጣይ ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆናሉ ሲሉም አሳስበዋል። በመሆኑም የአስር አመቱ መሪ እቅድ ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራትና እቅዱን ወደ መሬት አውርዶ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። በሚኒስቴር መስረያ ቤቱ የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው የከተማ ልማት በባህሪው በአንድ አካል ብቻ የሚስተካከል ሳይሆን የብዙ ተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል። እስካሁን ባለው ሂደት በተለይ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እንደ ቴሌ፣ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድና የመሳሰሉት ተቋማት በመናበብና በቅንጅት ባለመስራታቸው በርካታ ሃብት ሲባክን ይታያል ሲሉም ተናግረዋል። ይህም ህዝብና መንግስት የልማቱ ተጠቃሚና ተገልጋይ እንዳይሆን አድርጓቸዋል ብለዋል። በመሆኑም መሪ እቅዱ ለሁሉም የዘርፉ አካላት እንደ መሪ ሆኖ የሚያገለግል ስለሆነ በአንድ አገራዊ እቅድ በመመራት አንዱ የገነባውን አንዱ የሚያፈርስበት አሰራር መቅረት አለበት ሲሉም ተናግረዋል። እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ከተሞች ድምር የቆዳ ስፋት ከሃገሪቱ የቆዳ ስፋት ጋር ሲነፃፀር 0 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ነው። ይህም ከአለም አቀፍ አማካይ የከተሞች የቆዳ ስፋት ከሆነው 3 በመቶ ጋር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች የተጨናነቁ፣ መሰረተ ልማቶቻቸው ያልተሟሉና የስራ እድል ፈጠራ አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተነስቷል። እናም የከተሞች ልማት እድገትን ከማህበረሰቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ አመራር መፍጠር የግድ መሆኑን ተነስቷል።