የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ጥር 08/2012 (ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ቅዳሜና እሑድ ይካሄዳሉ። ነገ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከመከላከያ ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ እሁድ ደግሞ በክልል ከተሞች ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ሙገር ሲሚንቶ ከወላይታ ድቻ ሙገር ላይ ከረፋዱ 4፡00 ሠዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካሁን ያደረጓቸውን አምስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ሙገር ሲሚንቶ በ13 ነጥብ ሲመራ፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ወላይታ ድቻና መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ 11 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ያለምንም ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃ ይዟል። በሌላ የስፖርት ዜና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ። ነገ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች እና ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ በተመሳሳይ ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከሚዛን አማን ከተማ ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት፤ መከላከያ ከከምባታ ዱራሜ ከረፋዱ 4 ሠዓት ከ30 እንዲሁም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ ከረፋዱ 5 ሠዓት ከ30 ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ ቂርቆስ ከፍለ ከተማና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ1ኛ-4ኛ ደረጃን ይዘዋል። አዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን በ36 የግብ ዕዳ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።