በምርጫ እንቅስቃሴ ወቅት ሀሳባችንን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለህዝቡ ለማቅረብ እየስራን ነው-- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ እንቅስቃሴ ወቅት ሀሳባችንን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለህዝቡ ለማቅረብ እየስራን ነው-- የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ ፤ጥር 8/2012 (ኢዜአ) ወደምርጫ እንቅስቃሴ በምንገባበት ወቅት ሀሳባችንን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለህዝቡ ማቅረብ የሚያስችል ስራ እየከወን ነው ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። 6ኛው አገራዊ ምርጫ በተያዘው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትናንት በስቲያ አገራዊ ምርጫውን አስመልክቶ ጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በጊዜያዊው ሰሌዳ መሰረት ፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ዘመቻ ማካሄድ የሚችሉት ከሚያዚያ 27 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሆነም ያስቀምጣል። ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ይሆን ዘንድ ከመላው ዜጋ በተለይም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቀው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን የተለያዩ ወገኖች ሲገልፁ ይደመጣል። ኢዜአ በምርጫ እንቅስቃሴ ወቅት ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በምን አይነት መልኩ ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል? በዚህ ረገድ ፓርቲዎቹ ያላባቸው ሃላፊነት ምንድነው? ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ ወይ? በሚሉት ጉዳዮች ላይ የኦነግና ኢዜማ አመራር አባላትን አነጋግሯል። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖርን ግንኙነት እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ስርአት የቃል ኪዳን ሰነድ መጋቢት ወር 2011ዓ.ም ፖለቲካ ፓርቲዎች መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ዘለቀ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የሰፈሩትን አንቀጾች አስመልክቶ ለፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል። በዚሁ መሰረት የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ማንኛውም ግጭትና አለመረጋጋት ከሚፈጥር ነገር ተቆጥበው ሰላማዊ መንገድ ብቻ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ እያስተማሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ፓርቲው አባላቱንና ደጋፊዎቹን ስነ ምግባር በተሞላበት መልኩ እንቅስቃሴ እንዲያደጉ መልዕክት እያስተላለፈ መሆኑን አመልክተዋል። ግጭትን የሚቀስቀሱ ንግግሮች በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በኩል እንዳይሞከሩ አስፈላጊው ጥንቃቄ ይደረግ ዘንድም ኢዜማ እየሰራ መሆኑን ነው አቶ ናትናኤል የገለጹት። ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ የሆነ አካሄድ መከተል እንደሚገባቸው ተናግረዋል። "ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው" ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልፀዋል። ሆኖም ግን አሁንም ፓርቲዎች ለመንቀሳቀስ የሚገደቡባቸው ቦታዎች በመኖራቸው መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ብለዋል። መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ቢፈልግ ያንን ብቻውን ማድረግ እንደማይችል የሚናገሩት የኢዜማ ህዝብ ግንኙነት ኀላፊ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የፖላቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው ገልጸዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ፓርቲያቸው ሀሳቡን በሰለጠነ መንገድ አቅርቦ ለመከራከር ዝግጁ ነው ይላሉ። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ዓይነት የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በመጠቆም። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ልዩነታቸውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማራመድ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከስሜታዊነት ተቆጥበው ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ የማቅረብ ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ መንግስትና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በእጃቸው ላይ ያለ ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል። የመንግስት የጸጥታ መዋቅር እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በመውረድ በተደራጀ መልኩ ሰላምንና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ መስራት አለበትም ብለዋል።