ህጋዊ መንገድን ሳይከተል ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚፈጸም ብድር የከተሞች ዕዳ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ህጋዊ መንገድን ሳይከተል ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚፈጸም ብድር የከተሞች ዕዳ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ጥር 8/2012 (ኢዜአ) ህጋዊ የብድር ስርዓትን ሳይከተል ለከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ የሚፈጸም ብድር ለከተሞች ዕዳ እየሆነ በመምጣቱ ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አሳሰበ። የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ከተማ ጥር 6 እና 7 ቀን 2012 ዓ.ም ተገምግሟል። በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስፍን አሰፋ እንዳሉት፤ ህጋዊ የብድር ስርዓትን ሳይከተሉ ለከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ የሚፈጸሙ ብድሮች ለከተሞች ዕዳ ሆነዋል። በየጊዜው የስራ ኃላፊዎች መቀያየር ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት ማስመዝገብ እንዳላስቻለ አብራርተዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚሰጠው የገንዘብ ብድርና የመስሪያ ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ አይደለም። በቀጣይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን አደራጅቶ ወደ ስራ ለማስገባት በሚከናወኑ ተግባራት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። የስራ ዕድል ፈጠራ ዓላማ የዜጎችን ህይወት መለወጥ እንደሆነ የገለጹት አቶ መስፍን፤ ''በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ክልሎችና ከተሞች ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል'' ብለዋል። የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን በተጠናከረ መንገድ አለመስራት የአመራር ውድቀት ማሳያ ስለሆነ በዘርፉ ውድቀት እንዳያጋጥም ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ክልሎችና ከተሞች በስራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና ዙሪያ በሚያከናውኑት ተግባር ላይ ለሙስናና ለኪራይ ሰብሳቢነት በሚያጋልጡ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አቶ መስፍን አሳስበዋል። እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ዝቅተኛ የስራ አፈጻጸም የታየባቸው ክልሎችና ከተሞች ማካካሻ ዕቅድ አውጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል። እንዲሁም ባለፉት ስድስት ወራት መቶ በመቶ የዕቅድ አፈጻጸም የታየባቸውን የስራ ዘርፎች በቀሪው ግማሽ በጀት ዓመት ለመድገም ክለሳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ክልሎችና ከተሞች የዘርፉ ምክር ቤቶችን በማጠናከር የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አቶ ዘነበ አሳስበዋል። በብድር አሰጣጥና አመላለስ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎች የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅረበዋል። በመጨረሻም ለስራ ዕድል ፈጠራ በተዘጋጁ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች ላይ የሚታየውን የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ ዘነበ ጠይቀዋል።