ቀጥታ፡

የህፃናት መብት፣ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ በወጡ ህጎች አተገባበር ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዳማ፤ ጥር 8/2012 (ኢዜአ)የህፃናት መብት፣ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጡ ህጎች አተገባበር፣የሚዲያ ፕሮግራም ዝግጅትና አዘጋገብ ዙሪያ ለሚዲያ ባለሙያዎች የተዘጋጀ መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደተናገሩት የሚዲያ ተቋማት የነገይቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት በህፃናት ስብዕና ግንባታ ልዩ ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

ከአገሪቱ ህዝብ 30 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህን የኅብረተሰብ ክፍል በመልካም ሥነ ምግባር ማነፅ አገርን ማዳን ነው ብለዋል።

ከመደበኛ ትምህርት በፊት ህፃናት ስለ አስተዳደግና ስብዕና ግንባታ በቂ ግንዛቤ፣ክህሎትና እውቀት ማስጨበጥ ከተቋሟቱ  የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መሆኑን  አመልክተዋል።

መድረኩ የሚዲያ ባለሙያዎች የህፃናት ፕሮግራሞች ዝግጅትና አዘጋገብን  በውጤታማነት እንዲመሩ መዘጋጀቱን  አስታውቀዋል።

ልዩ ፍላጎት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት በተለይም ህፃናት በሚዲያው ትኩረት እንዳላገኙ ተናግረዋል።

የነገዋን የበለፀገች አገር ለመፍጠር የህፃናት ስብዕና ግንባታና የአዕምሮ ልማት ላይ በመስራት የህፃናት መብት፣ጥቅምና ደህንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ይገባናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሚዲያው ህፃናት በመልካም ስሥነ ምግባር እንዲታነፁና በጥሩ ስብዕና እንዲያድጉ ከማድረግ አኳያ ድርሻው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ቪክቶር ችያማ ናቸው።

ኢትዮጵያ ያሉት ከ15 ዓመት በታች የሆነ የኅብረተሰብ ክፍል የአገሪቷን ቀጣይ እጣፋንታ ለመወሰን ባለው ሚና በተቋማቱ  ትኩረት  ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ህፃናት መብታቸው፣ደህንነታቸውና ጥቅማቸው ዙሪያ ልዩ ጥበቃ እንዲያገኙና ፍላጎታቸውን መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ተቋማቱ ለፖለቲካ ሽፋን ከሚሰጡት ትክረት ጎን ለጎን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዕኩልነትና ፍትሃዊነት የማገልገል ግዴታ አለባቸው ያሉት ተወካዩ፣ ህፃናት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው አገር አቀፍ መድረክ ላይ ከግልና ፐብሊክ ሚዲያ ተቋማተ የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም