የቀነኒሳ እና የኪፕቾጌን የለንደን ማራቶን ፉክክር ዓለም በጉጉት እየጠበቀች ነው

145
አዲሰ አበባ ፤ጥር 8/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ኬንያዊው ኤልዩድ ኪፕቾጌ በዘንድሮው የለንድን  ማራቶን የሚያደርጉት ፉክክር አጓጊ ሆኗል። ቀነኒሳ የምንግዜም የዓለም ማራቶን ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን፥ ኪፕቾጌ ደግሞ የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ነው። የ37 ዓመቱ ቀነኒሳ ባሳለፍነው መስከረም በርሊን ላይ ባሸነፈበት ወቅት የኪፕቾጌን የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ለመስበር 2 ሰከንዶች ብቻ ነበር የቀሩት። “ከዚህ ቀደም ከኤልዩድ ጋር ብዙ ውድድሮችን አድርገናል፤ በቀጣይም እንደምንወዳደር አስባለሁ” ነው ያለው ቀነኒሳ። የለንደን ማራቶን ዳይሬክተር ሁፍ ብሬሸር  የብርቱዎችን እሽቅድምድም ለማየት ዓለም በጉጉት እየጠበቀች ነው ብለዋል። በውድድሩ ኢትዮጵያውያኑ ሞስነት ገረመው እና ሙሌ ዋሲሁን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። የ35 ዓመቱ ኤልዩድ ኪፕቾጌ በጥቅምት ወር ቬና ላይ በተካሄደው የማራቶን ሩጫን ከሁለት ሰዓት በታች የመግባት ታሪካዊ  ሩጫ ክብረወሰኑን መውሰዱ ይታወሳል። በወቅቱም ሩጫውን 1 ሰዓት ከ59 ደቂቃ ከ40  ሰከንድ በመግባት ታሪክ ሰርቷል። ኤልዩድ ኪፕቾጌ ከፈረንጆቹ 2013 ወዲህ 12 የማራቶን ውድድሮችን ያደረገ ሲሆን በ11ዱ አሸናፊ ሆኗል። ቀነኒሳ በቀለ እና ኤልዩድ ኪፕቾጌ ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 14 የትራክ ውድድሮች በ11ዱ ቀነኒሳ አሸንፏል። በጎዳና ላይ ሩጫዎች በተገናኙባቸው አራት የማራቶን ውድድሮች ሁሉንም ያሸነፈው ኪፕቾጌ ነው። ቢቢሲ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም