ቀጥታ፡

ሳዑዲ አረቢያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ይጠየቁ የነበረውን የመውጫ ቪዛ ውዝፍ መቀጮ ክፍያ አነሳች

አዲስ  አበባ  ጥር፣7/2012 (ኢዜአ) ሳዑዲ አረቢያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ በአገሪቱ የቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ይጠየቁ የነበረውን የመውጫ ቪዛ ውዝፍ መቀጮ ክፍያ ለስድስት ወራት ለማንሳተ ዛሬ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከስምምነት ላይ ደርሳለለች። ውዝፍ የመቀጮ ክፍያው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቤተሰብ አባላት ቁጥር በነፍስ ወከፍ እየተጠየቁ ሲከፍሉ መቆየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በህጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መጥተው በሚደርስባቸው የመብት ጥሰቶችና በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ ገበታቸው ጠፍተው የሚንቀሳቀሱና ኢቃማቸው(የመኖሪያ ፈቃዳቸው) የተበላሸባቸው እንዲሁም ቀይ ባህርን አቋርጠው ሳዑዲ አረቢያ ገብተው ወደ አገር መሄድ ያልቻሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን እስር ቤት ሳይገቡ የመውጫ ቪዛ ማግኘት የሚችሉበት ሕጋዊ አሰራር ባለመዘርጋቱ ምክንያት ከፍተኛ እንግልት ሲደርስባቸው እንደቆየ ተገልጿል። ይሄው ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ከሚመለከታቸው የሳዑዲ አረቢያ የሰራተኛና ማሕበራዊ ልማት ሚኒስቴር የሥራ ክፍሎች እና ከሳዑዲ የውጭ ጉዳይ የቆንስላ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ጋር በየወቅቱ ውይይት፣ የተለያዩ ጥረቶችና እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ መቆየቱም ተመልክቷል። ጥረቱ ተሳክቶና የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ባደረገው ትብብር ዜጎቹ ለሕገ-ወጥ ደላሎች ብዝበዛና አላስፈላጊ እንግልት ሳይዳረጉ የቲኬት ወጪያቸውን በራሳቸው ሸፍነው የመውጫ ቪዛ በማግኘት ወደ አገር ቤት እንዲሄዱ የሚያስችል ሕጋዊ አሰራር ተፈቅዶ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በተጨማሪም ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ሕጻናትንም በተመለከተ ወላጆች ከኤምባሲ የጉዞ ሰነድ(ሊሴ ፓሴ) እና የድጋፍ ደብዳቤ በመውሰድ ወደ ሳዑዲ ዲፖርቴሽን ማዕከል በመሄድ መውጫ ቪዛ አግኝተው ከልጆቻቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዲችሉ ኤምባሲው ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር በመነጋገር ባመቻቸው ሕጋዊ አሰራር ዜጎች በመጠቀም ላይ መሆናቸውንም ነው መግለጫው ያመለከተው። ይሁንና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ በሳዑዲ ዓረቢያ በቆዩ የሁሉም የውጭ አገር ዜጎች ላይ እየተተገበረ የሚገኘውና የመውጫ ቪዛ ለማግኘት በቤተሰብ አባላት ቁጥር በነፍስ ወከፍ በየወሩ ይጠይቅ የነበረው አራት መቶ የሳዑዲ ሪያል ውዝፍ መቀጮ ክፍያ በመብዛቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች በእድሉ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር። ኤምባሲውም ይኸው ክፍያ እንዲቀንስ ወይም እንዲነሳ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመንግስት አካላት ጋር በተደረገ ውይይትና ግፊት የውዝፍ ክፍያው ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህ ስምምነት በዋናነት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ ለቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ሮያል ኮርት በተሰጠ ምህረትና መመሪያ በልዩ ሁኔታ የተፈቀደ ሲሆን፣ ተግባራዊ የሚሆነውም በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ባለው ጊዜ ብቻ እንደሆነም ታውቋል። ይህንኑ የአጭር ጊዜ ዕድል ለዜጎች ለማዳረስ እንዲቻል በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ጅዳ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በተጨማሪ በመዲና፣ አብሃ፣ ጂዛን፣ ጣኢፍ ከተሞች ጭምር የጊዜያዊ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቸ ተከፍተው ሂደቱን ለማስጀመር ከሚመለከታቸው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። ዜጎች የጉዞ ሂደታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በስማቸው የተመዘገበ ተሽከርካሪ ካለ ወደ ትራፊክ ቢሮ በመሄድ ሃላፊነት ማውረድና በግላቸው የጉዞ ቲኬት የማዘጋጀት ሃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋልም ተብሏል። ስለሆነም በዚህ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ባለው ጊዜ ብቻ ተፈጻሚ የሚሆነውን እድል ኢትዮጵያዊያን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ኤምባሲው ማሳሳቢያውን አቅርቧል። ከሳዑዲ አረቢያ የፖሊስ፣ ሕግ አስፈጻሚና ጸጥታ አካላት ጋር በተደገረ ምክክር ኢትዮጵያዊያኑ  አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ጣቢያዎቹ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት አላስፈላጊ እንግልት እንዳያጋጥማቸው ሁኔታዎች የተመቻቹ መሆኑን ኤምባሲው መግለጹን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም