የኢትዮጵያ ብሄራዊ አክሬዴቴሽን ጽህፈት ቤት ህክምናን ጨምሮ በተለያዩ የቁጥጥርና ፍተሻ መስኮች ለተሰማሩ ሰባት ተቋማት የሥራ ፈቃድ ወይም አክሬዴቴሽን ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አክሬዴቴሽን ጽህፈት ቤት ህክምናን ጨምሮ በተለያዩ የቁጥጥርና ፍተሻ መስኮች ለተሰማሩ ሰባት ተቋማት የሥራ ፈቃድ ወይም አክሬዴቴሽን ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አክሬዴቴሽን ጽህፈት ቤት ህክምናን ጨምሮ በተለያዩ የቁጥጥርና ፍተሻ መስኮች ለተሰማሩ ሰባት ተቋማት የሥራ ፈቃድ ወይም አክሬዴቴሽን ሰጠ። ጽህፈት ቤቱ ፍቃዱን የሰጠው ባህርዳር ለሚገኙት ፈለገ ህይወት ኮንፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ለጋምቢ ጠቅላላ ሆስፒታል ላብራቶሪዎች እንዲሁም ጌዲዮ ለሚገኘው ለጌዶ ጠቅላላ ሆስፒታል ላብራቶሪና ለአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ጤና ምርምር ሪፈራል ላብራቶሪ ነው። በሰርተፊክሽን ዘርፍ ደግሞ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ በፍተሻ ላብራቶሪ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም በኢንስፔክሽን ዘርፍ፤ ኪው አይቲ ኤስ የተባለ ድርጅት የሥራ ፍቃድ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። አክሬዲቴሽን የተሰጣቸው የህክምና ተቋማቱ የላብራቶሪ ፍተሻ በመስጠት ህዝቡን በጥራትና በተገቢው መልኩ ከማገልገል ባሻገር ተጠቃሚውን ከተደጋጋሚ ምርመራ ወጪ ለመታደግ የሚያስችል ነው ተብሏል። የኢትዮጵየ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ደግሞ በኢንስፔክሽን ዘርፍ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ጥራት ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይችላል። ኪው አይቲ ኤስ የተባለው ድርጅትም የጨርቃጨርቅ፣ የፕላስቲክና የወረቀት ምርቶች ላይ የቁጥጥር ሥራ ለማናወን የሚያስችለው እውቅና አግኝቷል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አክሬዲቴሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ፍስሃ እንደገለጹት አክሬዲቴሽን የተሰጣቸው ተቋማቱ በትክከል አገልግሎቱን እየሰጡ መሆኑን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ፍተሻና ክትትል ይደረግባቸዋል። በዚህም መሰረት ድክመት ከታየባቸው ከጊዜዊ እገዳ ጀምሮ ሌሎች ከፍ ያሉ የእርምት እርምጃ ይወሳድባቸዋል ብለዋል። በሀገሪቱ በህክምና፣ በፍተሻ፣በኢንስፔክሽንና በሰርተፍኬሽን ዘርፎች 67 ተቋማት ስራ ላይ ያሉ ሲሆን 5 ተቋማት ደግሞ ጊዜዊ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ሌሎች ወደ 20 የሚጠጉ ተቋማት አክሬዴቴሽኑ የታገደባቸው መሆናቸውም ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል።