የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ51 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

63
ድሬዳዋ ኢዜአ ጥር 7 ቀን 2012 ብጥብጥና ሁከት በመፍጠር የመማር ማስተማር ስራን አስተጓጉለዋል ባላቸው 51 ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሥራ ጥር 18 ቀን 2012  እጀምራለሁ ብሏል። የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ለኢዜአ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ  እርምጃው ተወስዷል። "ተማሪዎቹ በሁከትና ብጥብጥ በመሳተፍ የመማር ማስተማር ስራው እንዲስተጓጎል ማድረጋቸው በዩኒቨርሲቲውና በህግ አካላት በመረጋገጡ እርምጃው ተወስዶባቸዋል" ብለዋል። እርምጃው ከተወሰደባቸው ተማሪዎች መካከል ሁለት ተማሪዎች  ለሁለት ዓመትና ሰባት ተማሪዎች ደግሞ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንደታገዱ አስረድተዋል። ቀሪዎቹ 42 ተማሪዎች የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ዶክተር ኡባህ  አስታውቀዋል። እንደ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ ታህሳስ 27 ቀን 2012  የተቀጡ 17 ተማሪዎችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት እርምጃ የወሰደባቸው ተማሪዎች ቁጥር 68  ደርሷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲው ''ኃላፊነታቸውን አልተወጡም'' ያላቸውን 17 የጥበቃ ሰራተኞች ከስራ ማሰናበቱንና የጥበቃ ኃላፊውንም ከደረጃ ዝቅ አድርጓል ብለዋል። በአስተዳደሩ ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም መምህራን ላይ ''ሰፊና ጥልቅ'' ግምገማ መደረጉን የገለፁት ዶክተር ዑባህ፣ በድርጊቱ ተሳትፎ በነበራቸው ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል ። ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ጥያቄዎችን ለመመለስ የተማሪዎች መኝታ፣ ምግብ ቤትና ህክምና መስጫ፣ ህንጻዎችን በማደስ የተቋረጠውን ትምህርት ለመጀመር  ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራ ጥር 18 ቀን 2012 ይጀምራል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም