ለሶስት የግብርና ሙያ ዘርፎች የስልጠና ስርዓተ-ትምህርት ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሶስት የግብርና ሙያ ዘርፎች የስልጠና ስርዓተ-ትምህርት ተዘጋጀ
አዳማ፤ ጥር 7/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ በወተት፣ በዶሮና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሙያ ደረጃዎች ሥረዓተ ትምህርት ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
የስርዓተ ትምህርቱ የማስተዋወቂያ መድረክ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት እንዳሉት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው።
በተለይ የስራ ገበያውን መሰረት ያደረገ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለኢንዱስትሪው ለማቅረብ ተገቢነትና ጥራት ያለው የስርአተ-ትምህርትና ማሰልጠኛ መሳሪያዎች በወቅቱ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ኤጀንሲው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ገበያውን መሰረት ያደረጉ የሙያ ደረጃዎች በወተት ልማት፣በዶሮና በአትክልትና ፍራፍሬ የሙያ መስኮች ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን ጥቅሰዋል።
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አሰልጣኞች ከተለያዩ ሀገራት ልምድን ቀስመው በዝግጅቱ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸው “በተለይ በካናዳ መንግስት የተቋቋመው አትስቬ (ATTSVE) ፕሮጀክት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል”ብለዋል።
“በዚሁ የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝ በሶስቱ የሙያ መስኮች ከአንድ እስከ አራት የሙያ ደረጃ፣የስርዓተ ትምህርት፣የማሰልጠኛ መሳሪያዎችና የምዘና መሳሪያ ዝግጅት ተጠናቋል”ብለዋል።
ከ91 በላይ የማሰልጠኛ መማሪያ ሰነዶች በመዘጋጀታቸውም በቀጣይ ቀሪ ስራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ማስገባት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ስርዓተ ትምህርቱ ከአዲሱ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ከዚህ በፊት በትምህርት ጥራት፣አግባብነትና ወጥነት ላይ ያጋጠመውን ችግር ከመፍታት አንፃር ክልሎችና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
አትስቬ ፕሮጀክት ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ መሰለ ጫኔ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከካናዳ መንግስት በተገኘ 18 ሚሊዮን ዶላር ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት በኦሮሚያ፣አማራ፣ትግራይና ደቡብ ክልሎች እየሰራ ነው።
“ከነዚህ ክልሎች በተመረጡ ነጆ፣ወላይታ ሶዶ፣ወረታና ማይጨው ግብርና ና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገበያን መሰረት ያደረጉ የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ስርዓተ ትምህርቶችና የስልጠና ቁሳቁሶችን እንዲያዘጋጁ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ያተኮረው በኮሌጆቹ ተቋማዊ ለውጥ፣ የአካዳሚክ የአቅም ግንባታ ድጋፍና የኢንተርኔት ትስስር ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባለፉት አራት አመታት በዚህ ረገድ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል 379 ኮምፒውተርና 888 ለመማር ማስተማር የሚያግዙ መጸሀፍት ለኮሌጆቹ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ከኮሌጆቹ ለተውጣጡ 65 መምህራንም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የመጀመሪያና የሁለተኛ ድግሪ የትምህርት እድል መመቻቸቱን አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ 271 ተመራቂ ተማሪዎች ተወዳዳሪ የሆነ ፕላን አዘጋጅተውና በ60 አነስትኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ስራ ውስጥ እንዲገቡም የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።