የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በዘርፉ አስፈጻሚዎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በዘርፉ አስፈጻሚዎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ገለፀ
ጥር 7/2012 ኢዜአ የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በ11 ከተሞች ባሉ የዘርፉ አስፈጻሚዎች የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ማረጋገጡን አስታወቀ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት ወደስራ ያልገቡ 492 ሼዶች እና 8 ህንጻዎች መኖራቸውን ኤጀንሲው ጠቁሟል።
የኤጀንሲው የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ትናንት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
ኤጀንሲው የመስክ ምልከታ ባካሄደባቸው ከተሞች በአንድ ማዕከላት ውስጥ አገልግሎት መስጠት የሚገባቸው ባለሙያዎች በስራ ሰዓት ባለመገኘታቸው በድጋፍ አሰጣጡ ላይ ማነቆ መፍጠሩን ባቀረበው ሪፖርቱ አመልክቷል።
የዘርፉ ባለሙያዎች በስራ ገበታቸው ላይ አለመገኘት ስራ ፈላጊዎች እና ተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉ በመስክ ምልከታ መታየቱ ተገልጿል።
አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደስራ መግባት ይችሉ ዘንድ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ከፌዴራል የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ በኩል የሚጠየቁት የአገልግሎት ክፍያ የስራ ፈላጊዎችን አቅም ያላገናዘበ እንደሆነም ሪፖርቱ አመልክቷል።
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር የኤሌትሪክ ኃይል ለሚያስፈልጋቸው የመስሪያ ቦታዎች የትራንስፎርመር ክፍያ የተፈጸመ ቢሆንም የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት በወቅቱ ባለመሟላቱ የመስሪያ ቦታዎቹ ያለአገልግሎት መቀመጣቸውንም ሪፖርቱ አትቷል።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአስሩም ክፍለ ከተሞች በመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት ወደ ስራ ያልገቡ 492 ሼዶች እና 8 ህንጻዎች እንዳሉም ተጠቁሟል።
በትግራይ ክልል የተላለፉ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች የአስተዳደር ስርዓት ክፍተት ያለባቸው መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል። የተላለፉትን ለማስመለስና አዲስ ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ለማስተላለፍ በቅንጅት የመስራት ችግር እንዳለም በመስክ ምልከታው ተረጋግጧል።
በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሀዋሳ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ በኩል ግንባታቸው የተጀመረ የመስሪያና የመሸጫ ህንጻዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ለመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ 25 የመስሪያ ቦታዎች፣ በአማራ ክልል 493 ሼዶች እና 670 ኮንቴነሮች፣ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ 16 ሼዶችን በማስለቀቅ ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች መተላለፋቸውም ተገልጿል።
በክልሎችም ከአሰራር ስርዓት ውጪ የተያዙ ሼዶች አለመመለሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው እንደቀጠሉ ሪፖርቱ አመልክቷል።
የብድር አቅርቦት እጥረት እና የብድር ዋስትና አማራጮች የስራ ፈላጊዎችን አቅም ያላገናዘቡ መሆንም ጥያቄ እንደሚነሳበት ተገልጿል።
በተለይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና የመኪና ሊብሬ እንዲሁም በአዲስ አበባ ነባር ኢንተርፕራይዞች ደረቅ ቼክ መጠየቅ በመስክ ምልከታው መረጋገጡ ተጠቅሷል።
በሐረሪ ክልል የብድር አገልግሎቱ በተገቢው መንገድ አለመሰራጨቱንና የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ለማይመለከታቸው ማህበረሰብ ክፍሎች መስጠቱም እንዲሁ።
በኦሮሚያ ክልል ያለውን የማዕድን ሀብት ለስራ ፈላጊዎች የገበያ ዕድል እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆኑ መምጣታቸው ተጠቅሷል።
የመስክ ምልከታ በተደረገባቸው በሁሉም ክልሎችና ከተሞች የመልካም አስተዳደር እና ኪራይ ሰብሳቢነት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ከመግባት አንጻር ዝግጅት ቢኖርም የአፈጻጸም ችግር እንዳለ ሪፖርቱ አመልክቷል።
በሌላ በኩል የመደበኛ የግንኙነት ጊዜ ጠብቆና የጋራ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወጥነት ባለው ሁኔታ ስራዎችን እየገመገሙ እና አቅጣጫ እያስቀመጡ ከመምራት አኳያ በሁሉም ክልሎችና ከተሞች ክፍተት እንዳለ በግምገማው ተረጋግጧል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች የደህንነትና የስራ መሳሪያ አቅርቦት የወቅታዊነት፣ የጥራት እና የመጠን ችግሮች እንዳሉም በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
በሀዋሳ ከተማ በምግብ ዋስትና ፕሮግራም የሚታቀፉ ዜጎች የምልመላና መረጣ ስራውን ኃላፊነት በውል አለመገንዘብና ፍትሃዊ ያልሆነ የምልመላ ስራዎች መከናወናቸውም ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ በዘርፉ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ክልሎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን በሰው ኃይል፣ በግብዓት እና በበጀት መደገፍ እንዳለባቸው የመፍትሄ ሀሳብ ቀርቧል።
እንዲሁም ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በማዕከላት ገብተው ለስራ ፈላጊዎች የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።
በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ሼዶችን ወጥነት ባለው ንቅናቄ እና የአሰራር መመሪያ ማስለቀቅ እንደሚገባም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በፌዴራል ደረጃ ደግሞ በዘርፉ ስትራቴጂና የድጋፍ ማዕቀፎች ላይ ለክልል አመራሮች እና ባለሙያዎች በቂ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እንደሚገባም ተገልጿል።
እንዲሁም የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም መከለስ እንደሚያስፈልግም ሀሳብ ቀርቧል።
ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች በፌዴራል የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ በኩል ህጋዊ ዕውቅና ለማግኘት የሚከፈለው የአገልግሎት ክፍያ አቅምን ያገናዘበ እንዲሆን ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።
በመጨረሻም ከኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ከክልልና ከሚመለከተው ተቋም ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባም ሪፖርቱ ጠቁሟል።