ቀጥታ፡

የአጼ ቴዎድሮስን መርህ በመከተል ለህዝቦች አንድነት መጣር እንደሚገባ ተገለጸ

ጎንደር ጥር 7/2012 /ኢዜአ/ የአጼ ቴዎድሮስን ፈለግ በመከተል ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት መረጋገጥ ጥረት እንዲደረግ የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። የአፄ ቴዎድሮስ 201ኛ ዓመት የልደት በዓልን በማስመልከት በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በወቅቱ እንደገለጹት አጼ ቴዎድሮስ በመፈረካከስ አደጋ ላይ የነበረች ኢትዮጵያን ለመመለስ የፈጸሙት ተጋድሎ በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው። የዘመነ መሳፍንት እየተባለ የሚታወቀው ስርዓት ጉልበተኞች ህዝቡንና አገሪቱን በመከፋፈል ቀደምት የነበረውን ስልጣኔ ወደ ኋላ የመለሱበት ጊዜ እንደነበር ጠቅሰዋል። "በወቅቱ ወደ ስልጣን የመጡት አጼ ቴዎድሮስ አገሪቱን አንድ ከማድረግ ባለፈ በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ የበለጸገች ለማድረግ ያስቀመጡት ጉልህ አሻራ እስካሁን የሚዘከር ነው" ብለዋል። "አሁን ላይ ያለን ትውልዶች በአላማችን የፀናን፣ ሰውን በሰውነቱ የምንለካ፣ ሰላም ወዳድና ለጋራ አንድነት መስዋዕት የምንከፍል ከሆን የንጉሰ ነገስቱን ታሪክ ለመዘከር ብቁ ነን" ሲሉም ተናግረዋል ። ወጣቱ ትውልድ የእርሳቸውን ተጋድሎና የብልጽግና ፍላጎት ከታሪክ በመማር በተጀመረው የለውጥ ጉዞ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል። "የአንድነትንና የጥንካሬን መንገድ ብቻውን ጀምሮ የተሳካለትን ታላቅ መሪ መዘከር ታላቅ ጸጋ ነው" ያሉት ደግሞ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር በሪሁን ካሳው ናቸው፡፡ "በመሆኑም ንጉሰ ነገስቱ ከሰሩት አኩሪ ታሪክ በመማር አሁን ላይ ከገጠመን አገራዊ ችግርና ፈተና ለመላቀቅ አዲስ ታሪክ መስራት ይገባናል" ብለዋል። አጼ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅና ዘመናዊ አገር ለመገንባት ህልም ሰንቀው የተነሱና ያለፉ መሆናቸውን በመግለጽ የአሁኑ ትውልድ አገራዊ አንድነትን ለማምጣት ተግቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በውይይት መድረኩ "የኢትዮጵያ አንድነትና ፈተናዎቹ" በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ታያቸው ናቸው፡፡ ባለፉት ክፍለ ዘመናት አገሪቱ ፈተናዎች ማስተናገዷን በጽሁፋቸው ያስታወሱት ምሁሩ፣ ትውልዱ በአገሪቱ ታሪክ አኩሪ ገድል ሰርተው ያለፉትን መሪዎች ፈለግ በመከተል ለጋራ ዓላማና አንድነት መስራት እንዳለበት አመላክተዋል። የአጼ ቴዎድሮስ የልደት በዓል በስዕል ኤግዚቢሽንና በፎቶ አውደ ርዕይ፣ ሀውልታቸው በቆመበት ስፍራ በሻማ ማብራትና የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ እንዲሁም በከተማው ዋና ጎዳናዎች በሚደረግ የአዝማሪ ማርሽ ስነ ስርዓት እንደሚከበር የወጣው መርሀ ግብር አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም