የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከደብሊን ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመርኩት ግንኙነት ተጠቃሚ አድርጎኛል አለ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከደብሊን ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመርኩት ግንኙነት ተጠቃሚ አድርጎኛል አለ
ሶዶ፤ ጥር 7 /2012( ኢዜአ ) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከአየርላንዱ ደብሊን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጀመረው ግንኙነት ተጠቃሚ መሆኑን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ኩማ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከአጋሩ ጋር በፈጠረው ግንኙነት የመማር ማስተማሩን ሂደት ውጤታማ እያደረገ ነው።
በዩኒቨርሲቲ እገዛ ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘው ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የቤተ-መጻህፍት አደረጃጀትና አያያዝ፣ የኮምፒዩተር ግብዓት፣ መረጃን በአንድ ማዕከል ማደራጀትና የሰው ኃይል ማበልጸግ ከሥራዎቹ ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከሰው ሃብት ልማት አንጻር ከ80 በላይ ምሁራን በዩኒቨርሲቲው ስልጠና መከታተላቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ዓለም አቀፍ ልምድ ለመቅሰምና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በቀጣይም በባህልና በቱሪዝም፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በምግብ ዋስትናና በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፎች ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር ግቢ ዲዛይን በማሻሻልም መልካም የመማሪያና የመዝናኛ አካባቢን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ብርሃኑ አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲዉ ከአጋር አካላት ጋር የሚደረገዉን ግንኙነት በማጠናከር ልምዶችን በምርምርና በፈጠራ ለማገዝና የአከባቢዉን ማህበረሰብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራ የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ናቸው።
የዩኒቨርሲቲዎቹ ግንኙነት የተገመገመበት ጉብኝት ሰሞኑን በወላይታ ሶዶ ተካሂዷል።