ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
ኢዜአ ጥር 6/2012... ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ያለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥሪ አቀረበ። የምርጫ 2012 ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮ አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩ የጊዜ ሰሌዳው ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ምርጫውን ለማስፈጸም ታቅዶ መዘጋጀቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል። ከታህሳስ 22 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ማደራጃ እንዲካሄድ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ቀርቧል። የካቲት 24 የምርጫ ክልል ካርታ ይፋ ማድረጊያ፣ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድ እንዲሁ። የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረቢያና መወሰኛ ጊዜ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የዕጩ ምዝገባ ጊዜ ከሚያዚያ 13 እስከ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑን ረቂቀ የጊዜ ሰሌዳው ያሳያል። የምረጡኝ ዘመቻ ደግሞ ከሚያዚያ 27 እስከ ነሃሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን እንዲሁም የዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረጊያ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን ረቂቀ የጊዜ ሰሌዳው ያመላክታል። የምረጡኝ ዘመቻ የሚከለከልበት ጊዜ ደግሞ ከነሃሴ 6 እስከ ነሃሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑንም ያሳያል። የድምጽ መስጫ ቀን ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን፤ በምርጫ ክልል ደረጃ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ከነሃሴ 11 እስከ ነሃሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ከነሃሴ 11 እስከ ነሃሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ሆኖ ቀርቧል። በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው እና አፈፃፀሙ ላይ ውይይት ያካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጊዜ ሰሌዳው ላይ ያላቸውን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከአስተያየቶቹም መካከል አገሪቱ አሁን ያላት የፀጥታና ደህንነት ጉዳይ አስጊ በሆነበት ሁኔታ ምርጫውን ማካሄድ ተገቢ አይደለም የሚል ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ፓርቲዎች ቢኖሩም ምርጫው በታቀደለት የጊዜ ገደብ መከናወን ይገባዋል ያሉም አሉ። የህዝብና ቤት ቆጠራ ሳይካሄድ እንዲሁም ህዝቡ ለምርጫ በቂ የስነ ልቦና ዝግጅት ሳያደርግ ምርጫውን ማካሄድ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት ተሰጥቷል። በሌላ በኩል ምርጫው ይካሄድበታል ተብሎ የተየዘለት የጊዜ ገደብ ክረምት ላይ በመሆኑ ይህ ደግሞ የአርሶና አርብቶ አደሩን ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል የሚልም ይገኝበታል። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት ምላሽ ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ መንግስት የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጥር በህግ ሃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል። ቦርዱም መንግስት የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ያስከብራል በሚል መነሻነት ምርጫው እንዲካሄድ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አንስተው ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ያለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። ምርጫው ይራዘም የሚለው ግን የህግ ጥሰት የሚፈጥር በመሆኑ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሄድ እንዳለበት አሳስበዋል።