የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ፖለቲካዊ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ፖለቲካዊ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ፤ጥር 6/2012 (ኢዜአ) የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ፖለቲካዊ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ። በኢትዮጵያ ለ27ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የተከበረውን የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን አከባበር የማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል። በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደሚነሳው ሁሉ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተለያዩ ሕጎችና ድንጋጌዎች ቢኖሩም ተግባራዊነቱ ላይ ክፈተቶች መኖራቸው አሁንም ተነስቷል። በተለይም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በተቋማት ተካቶ መሰራት ያለበትን ያህል እየተሰራ እንዳልሆነም ተጠቁሟል። ስራ ላይ ያሉ መጓጓዣዎችና የሚሰሩ ህንጻዎች ለአካል ጉዳተኛው ምቹ አለመሆንና በስራ ቦታዎች ላይ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው 'የአይችሉም ግምት' ዛሬም ድረስ መፍትሄ እንዳላገኘ ተጠቁሟል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ እንደተናገሩት፤ ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸውን ችግር ለማቃለል እየሰራ ይገኛል። በተለይም ህብረተሰቡ ስለ አካል ጉተኝነት ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መከናወን መቻላቸውን ገልጸዋል። የፌዴሬሽኑ አባል ማህበራት እንዲጠናከሩ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል። ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በበመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን በአብነት አንስተዋል። በአሁኑ ወቅትም በመጪው ምርጫ አካል ኩዳተኞች ተሳትፎ እንዲጎለብት እየተሰራም ነው ብለዋል። አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ለማቃለል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን ያልሸሸጉት አቶ አባይነህ፤ የአካል ጉዳተኞች ችግር የፖለቲካ ትኩረት ካላገኘ ውጤት ማምጣት አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል። ''የፖለቲካ ትኩረት ለአካል ጉዳተኞች ቢሰጥ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ'' ብለዋል። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት ያለበትን ክፍተት በማረም የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ማጽደቋን አስታውሰው የአፍሪካ አካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮል ለማጽደቅ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። የአካል ድጋፍ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመተባበር የዊልቸርና ሌሎች የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል። ለአብነትም ከህንድ መንግስት ጋር በመተባበር 600 ዜጎች የአካል ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ኤርጎጌ ገለጻ፤ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የአካል ጉዳተኞችን አካተው እንዲሰሩ ሚኒስቴሩ የተፈራረመውን ስምምነት ተግባራዊነት የሚከታተልም ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል። የተዘጋጀው የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ መንግሥት ትኩረት መስጠት መጀመሩን እንደሚያመላክትም ተናግረዋል።