የምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው ምርጫ ቦርድ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው ምርጫ ቦርድ አሳሰበ
አዲስ አበባ ፤ጥር 6/2012 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት የምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ። ቦርዱ ዘንድሮ በሚካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ እየተወያየ ነው። ቦርዱ አሁን ላይ የ'ምረጡኝ' ቅስቀሳ የጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትክክል አለመሆናቸውን በማስገንዘብ ከቅስቀሳ ዘመቻቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቅስቀሳ ሁሉም ፓርቲዎች ቦርዱ ባወጣው የምረጡኝ ዘመቻ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። በመሆኑም አሁን ላይ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎች ከዚህ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ መመሪያ አስተላልፈዋል። ይሄን በሚተላለፉ ፓርቲዎች ላይ ቦርዱ አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል። ቦርዱ ባወጣው ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ስሌዳ መሰረት የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ የሚካሄደው ከሚያዚያ 27 እስከ ነሀሴ 5 2012 ዓ.ም ነው።