ቀጥታ፡

በኤሌክትሪክ ሃይል  መቆራረጥ እና በመለዋወጫ  እቃ እጦት  የተሟላ አገልግሎት  እየተሰጠ አይደለም

አዲስ አበባ፤  ጥር/2012 (ኢዜአ) የከተማዋ ቀላል ባቡር በኤሌክትሪክ ሃይል  መቆራረጥ   እና  በመለዋወጫ  እቃ እጦት ምክንያት የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ችግሮቹ የሚስተዋሉ ቢሆንም የከተማዋ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የትራንስፖርት  ችግር በመቅረፍ በኩል ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሆነ  ተገልጋዮች  ይናገራሉ።

በጠመንጃ ያዠ የባቡር ፌርማታ ባቡር ሲጠብቁ  ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ  ሙሉቀን  ዳኛቸው እንዳሉት ጠዋት ወደ ስራ ለመሄድ  እና ከስራ  ለመመለስ  የባቡር  ትራንስፖርት ቀዳሚ ምርጫቸው ነው።

የባቡር ትራንስፖርት ከሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች በዋጋም ሆነ በፍጥነት የተሻለ  እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ሙሉቀን፤ ባቡሩ  በየፌርማታው በየ10 ደቂቃው ይደርሳል  ተብሎ የተነገረው ተግባራዊ አለመሆኑና የመዘግየት ችግር እንዳለበትም  አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በአንድ ባቡር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳፋሪዎች የሚጫኑ በመሆኑ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች  እና ለአቅመ  ደካሞች  አገልግሎቱ ምቹ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በታክሲ ሰልፍ ተማረው  የባቡር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሙሉ ገ/ኪዳን፤ ከዚህ ቀደም ከሚኖሩበት ፒያሳ ወደ ስራ ለመሄድ ቢያንስ ለ40 ደቂቃ ታክሲ ለመጠበቅ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

የባቡር ትራንስፖር መጠቀም ከጀመሩ ግን 15 ደቂቃ ባልበለጠ ግዜ ውስጥ ወደ ሥራቸው መሄድ እንደቻሉም ነው የገለጹት።

አንድ ባቡር ከመጠን በላይ በርካታ ተሳፋሪዎችን እየጫነ በመሆኑ  ከፍተኛ መጨናነቅ ይፈጠራል  ያሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ ይህ ደግሞ ለስርቆትና ለተለያዩ የጤና እክል የማጋለጥ እድሉ ሰፊ እንደሆነም ስጋታቸውን አንስተዋል።

በሃይል መቆራረጥ ችግር እና በመለዋወጫ እቃ እጦት ምክንያት  ተልእኮውን  እንዳያሳካ  እንቅፋት  እንደሆነበት  የአዲስ  አበባ ቀላል  ባቡር   የትራንስፖርት  ዲፓርትመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ አክሊሉ  ኢቢሶ ተናግረዋል፡፡

በመለዋወጫ እቃ እጦት ምክንያት በብልሽት ሥራ ያቆሙ 7 ባቡሮችን ወደ ስራ ማስገባት  እንዳልተቻለ  ገልጸው፤ በቀሪዎቹ 33 ባቡሮች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እየተሞከረ ነው ብለዋል፡፡

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ  ቀደም ብሎ የነበረውን  የመዘግየት  ችግር  ለመቅረፍ  በተወሰደው እርምጃ   ካለፈው ነሃሴ ወር ጀምሮ  በሁለት መስመር  ያሉት  ባቡሮች  በየ10  ደቂቃ  በፌርታ እንዲገኙ መደረጉን ነው አቶ አክሊሉ የገለጹት።

እነዚህ መሻሸሎች ቢኖሩም አልፎ አልፎ   በሃይል መቆራረጥ  እና በቴክኒክ  ችግር ምክንያት  በተለይም   ከፍተኛ መጨናነቅ  በሚስተዋልባቸው አከባቢዎች የመዘግየት  ችግር  እያጋጠመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የባቡር የመለዋወጫ እቃ ችግርን ለመቅረፍ ዓለም አቀፍ የግዢ ጨረታ ወጥቶ  በሂደት ላይ መሆኑንም  ገልጸዋል።

ቀደም ብሎ “በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የተገጠሙ የፓወር ገመድ (ኬብሎች)  ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት በመሆናቸው ሙሉ  ለሙሉ  ለመቀየር  እየተሰራ ነው” ያሉት አቶ አክሊሉ ችግሩን ለመፍታትም ከኢትዮጵያ መብራት ኃይል ጋር  በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

አንድ ባቡር 256 ሰዎች የመጫን አቅም ያለው ቢሆንም አሁን ግን እስከ 317 ሰዎችን  እየጫነ  ነው ያሉት አቶ አክሊሉ፤ ከስራ ውጭ የሆኑት ባቡሮች  ወደ ስራ ሲገቡ ችግሩን በከፊል  እንደሚቀረፍ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም