የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምዕመናን የጥምቀት በዓልን በሰላምና በእርጋታ እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረበች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምዕመናን የጥምቀት በዓልን በሰላምና በእርጋታ እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረበች

ኢዜአ፤ጥር 5/2012 የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲያልፉ ምዕመናን በእርጋታና በሰላም እንዲያከብሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጥሪ አቀረበች። የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት የሚታሰብበት በዓል ነው። የጥምቀት በአል ከዋዜማው የከተራ በአል ጀምሮ ጥር 11 በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስነ-ስርአቶች ነው የሚከበረው። ዘንድሮ የጥምቀት በዓል የሚከበረው በዓሉ በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዳሉት፤ ሰሞኑ ቤተክርስትያኗ አበይት በዓላትን የምታከብርበት ነው። ከበዓላቱ መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም መከበሩን አውስተው ጥምቀትና ቃና ዘገሊላን በዓላት በቅርቡ የሚከበሩ መሆኑን አውስተዋል። በመሆኑም ምዕመናን በዓላቱን በሰላምና ተረጋግተው እንዲያከብሩ ነው ፓትሪያሪኩ ጥሪ ያቀረቡት። የፀጥታ አካላትም የተለመደ ሰላምን የማስጠበቅ ተግባራቸውን አሁንም እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋም ተናግረዋል።