ሀገራቱ በንግድና ወንጀል መከላከል በጋራ መስራታቸው በቀጠናው ሰላም እንዲኖር ያስችላል-ም/ር/መስተዳድር ሙስጠፌ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራቱ በንግድና ወንጀል መከላከል በጋራ መስራታቸው በቀጠናው ሰላም እንዲኖር ያስችላል-ም/ር/መስተዳድር ሙስጠፌ
ኢዜአ ጥር 5/2012 ኢትዮጵያና ጅቡቲ በድንበር ንግድና ወንጀል መከላከል ጉዳዮች በጋራ መስራታቸው ለቀጠናው ህዝቦች ጥቅምና ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ። 26ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሯል። ስብሰባው አገሮቹ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እንዲሁም በንግድና ፀጥታ ጉዳዮች በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሆነ ተመልከቷል። የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ እንደገለጹት የአገሮቹ ህዝቦች የሚጋሯቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ጂቡቲና ኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ብቻ ሳይሆኑ፤ ወንድማማች ህዝቦች ያሉባቸው መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። አገሮቹ በንግድና ወንጀል መከልከል ጉዳዮች በጋራ መስራታቸው ለቀጠናው ህዝቦች የላቀ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል። አገሮቹ በድንበር ንግድና ወንጀል መከላከል በጋራ መስራታቸው በቀጠናው አካባቢ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ለህዝቦች የጋራ ጥቅም መጠበቅ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኰንን ናቸው። ስብሰባው በተለይም በቀጠናው ከፍተኛ አደጋ እየፈጠረ ያለውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ተያያዥ ወንጀሎች ለማስቀረት አገሮቹ በጋራ የሚሰሯቸውን ስራዎችን የሚያጎለብቱ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል። የጂቡቲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርና የልዑክ ቡድኑ መሪ ሙሚን አህመድ ሰብሰባው የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል። ለሦስት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ የአገሮቹ የመከላከያና ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖችና የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ጨምሮ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።