ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ከዘመናዊ ህግ ጋር ማስኬድ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ከዘመናዊ ህግ ጋር ማስኬድ ያስፈልጋል
ኢዜአ፤ጥር 5/2012 ኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ከዘመናዊ ህግ ጋር አብራ እንድታስኬድ የሰላም አባቶች መከሩ። የ82 አመት እድሜ ባለጸጋው አቶ ዘለቀ አርጃሞ በህይወት ዘመናቸው የፍርድ ቤትን ደጃፍ ረግጠው አያውቁም። ወደ ህግ የሚያደርስ ጉዳይ ሳይገጥማቸው ቀርቶ እንዳልሆነ ግን ወደ ኋላ መለስ ብለው ያደጉበትን ስርአት ያስታውሳሉ። ትውልዳቸው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን ሲሆን ከቤተሰብ ጀምሮ ለሚፈጠር ጸብ የራሱ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት እንዳለ ያወሳሉ። በአካባቢያቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ጸብ የሚፈታበት "ኡሩሻ" የተሰኘ ባህላዊ የቤተሰብ የእርቅ ስርዓት አለ። ከቤተሰብ አለፍ ሲልም ሰዎች ወደ ግጭት እየገቡ ማለፍ በአካባው አጠራር "ጎሜ" ወይንም ሃጢያት መሆኑን ያነሳሉ። በተጋጪዎች መካከል ገብቶ ለምለም ሳር፣ ኩታ ወይንም ጋቢ፣ የእንስሳት ቆዳና ሌሎች የጸብ ማብረጃ ተብለው የሚታወቁትን በመያዝ እንዲበርድ ያደርጋል። በባህሉ መሰረት ጸብን ለማብረድ እድሜ አይጠይቅም ይህንን አልፎ ወደ ግጭት መግባት ደግሞ "ጎሜ" ነው። ወደ ግጭት ሊያመሩ የነበሩ ግለሰቦች ተረጋግተው "ዱቡሻ" ወደተሰኘ የግጭት አፈታት ስርአት በመሄድ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል። ግጭት ወደ ሁከት ከማምራቱ በፊት የመከላከል ተግባር በዱብሻ የተሰየሙ አባቶች ተግባር ሲሆን በስርአቱ የሰውን ንብረት መዝረፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሰውን መግድል፣ ጸብ ማጫር የተወገዘ ነው። የእድሜ ባለጸጋው አቶ ዘለቀ አርጃሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዚህ ባህላዊ የእርቅ ስርአት በመፍታት ወደ ህግ ያልሄዱበትን ምክንያት አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም የጋሞ የሰላም አባት በመሆን በዱቡሻ የእርቅ ስርአት ውስጥ እያገለገሉ ሲሆን ከአባቶች የወረሱትን ባህል ለአዲሱ ትውልድ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል። የጋሞ ብሔረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት አሁንም በአካባቢው እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ እንደየአካባቢው ባህልና ወግ መሰል የግጭት አፈታት ያላት በመሆኗ መንግስት ከዘመናዊ የህግ ስርአት ጋር በማዋሃድ ቢተገብረው የሚፈጠሩ ችግሮችን ከጅምሩ መፍታት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው። ሌላው አባት አቶ ተስፋዬ ሻቃ በ2011 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ሊከሰት የነበረውን ግጭት እንዲረግብ ካደረጉ የጋሞ የሰላም አባቶች መካከል አንዱ ናቸው። እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት አንጻር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን የመቀነስ አቅም አላቸው። ኢትዮጵያ የተለያዩ የግጭት አፈታት ያሏትና ህብረትን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ መቀራረብን የሚሰብኩ እሴቶች ባለቤት ሆና ግጭት ሊበረታባት እንደማይገባ በቁጭት ያነሳሉ። በመሆኑም በነዚህ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ያደገ ወጣት የአባቶችን ምክር እንዲሰማ ጠይቀው መንግስትም እሴቱን እንዲጠቀምበት መክረዋል። የጋሞ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዘነበ በየነ ''የጋሞ ባህላዊ የእርቅ ስርአት በአካባቢው ጸብን በማብረድ ሚናው የጎላ ነው'' ብለዋል። ባህሉን ለሌሎች አካባቢዎችና ለአዲሱ ትውልድ ለማስተዋወቅ የህትመትና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ መሆኑን ሃላፊ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከራሷ አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሰላምን ለማውረድ የሚጠቅሙ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እንዳሏት ያነሳሉ። እነዚህን ባህላዊ እሴቶች ከዘመናዊ የህግ ስርአት ጋር በማቀናጀት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። የእሴቱ ባለቤት የሆኑ እናቶች እና አባቶች፣ ምሁራን፣ ባህልና ቱሪዝም፣ ህግ አውጪዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት እንዲዳብር መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።