ቀጥታ፡

በ2020 የአሎምፒክ የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ሊካሄድ ነው

ኢዜአ ጥር 5/2012 በሴኔጋል ዳካር በሚካሄደው የ2020 ኦሎምፒክ የቦክስ የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ውድድር ይካሄዳል። እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛ ኦሎምፒክ በቦክስ ውድድር አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት ከየካቲት 9 እስከ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል። በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ቦክሰኞችን ለመምረጥ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም የማጣሪያ ውድድር ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚካሄደው በዚህ ውድድር ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በ52 ኪሎ ግራም ወንድ የአዲስ አበባ ፖሊሱ ዳዊት በቀለ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ያዕቆብ በለጠ፣ በ57 ኪሎ ግራም ወንድ ፍቅረማርያም ያደሳ ከአዲስ አበባ ፖሊስ አብዱልሰላም አቡበከር፣ ከድሬዳዋ ከተማ፣በ63 ኪሎ ግራም ወንድ የፌደራል ፖሊሱ ሳሙኤል ሙሉጌታ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶቹ አብርሃም ዓለም፣ በ69 ኪሎ ግራም ወንድ መስፍን ብሩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ቢንያም ተስፋዬ ከፌደራል ፖሊስና በ75 ኪሎ ግራም ተመስገን ምትኩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ባምላክ ደጉ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የጨዋታዎቹ አሸናፊዎች በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር እንደሚሳተፉ ነው አቶ ስንታየሁ የጠቆሙት። ቦክሰኞቹ ለመጨረሻው የመለያ ውድድር የተመረጡት በባለፈው ዓመት በተካሄዱ ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮችና በ2012 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ  በተካሄደው የመጀመሪያው የክለቦች ውድድር ያገኙትን ውጤት መሰረት በማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል። የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ባደረገው ስብስባ በ81 ኪሎ ግራም ወንድ ሰይፈ ከበደ ከአዲስ አበባ ፖሊስ በ51 ኪሎ ግራም ሴት አገሬ እማኙ ከጎንደር ከተማ በቀጥታ በማጣሪያው እንዲሳተፉ መወሰኑን ገልጸዋል። ኮሚቴው ይሄን የወሰነው ተወዳዳሪዎቹ ባላቸው ወቅታዊ ብቃት በኪሎ ዘርፉ ከነሱ ጋር የሚመጣጠን ተወዳዳሪ ባለመገኘቱ እንደሆነ አመልክተዋል። በማጣሪያው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች የአንድ ወር የዝግጅት ጊዜ እንደሚኖራቸውና ተወዳዳሪዎቹን የሚያሰልጥኑ አሰልጣኞችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ፌዴሬሽኑ ይፋ እንሚያደርግም ጠቁመዋል። በ2010 ዓ.ም በሞሮኮ ካዛብላንካ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች የቦክስ ሻምፒዮና ውድድር ኢትዮጵያ የሦስት ሜዳሊያዎች ባለቤት በመሆን አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። በዘርፉ እውቀት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማፍራት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ለተወዳዳሪዎች በአገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች እንዲሳተፉ እድል እየፈጠረላቸው ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም