ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ያሳድጋል- አቶ ተወልደ ገብረማርያም

ኢዜአ፤ ጥር 5/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሰሞኑን በአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት ከአፍሪካ አገራት ጋር  በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያሳድገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት በጊኒ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ደቡብ አፍሪካ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶስቱ የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትብብር ከማሳደግ አኳያ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል። "እኛ ትልቅ አየር መንገድ ነን፤ አየር መንገዱ አፍሪካን በከፍተኛ ሁኔታ ያስተሳሰረ ነው፤ ትስስሩን መፍጠር ለሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ትልቅ ፈተና የሆነባቸው ጉዳይ ነው" ብለዋል አቶ ተወልደ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምዕራብ አፍሪካ አገራት አየር መንገድ የሆነውና መቀመጫውን በቶጎ ያደረገው አስካይ አየር መንገድ፣ ለማላዊ፣ ሞዛምቢክና ኢኮቶሪያል ጊኒ አየር መንገዶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ከዛምቢያና ጋና አየር መንገዶች ጋር በትብብር ለመስራት ውይይት መጀመሩንም ገልጸዋል። አየር መንገዱ ከአፍሪካ አገራት ያለው ግንኙነት በውድድር ላይ ሳይሆን በትብብር መስራት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ነው አቶ ተወልደ የሚናገሩት። የጊኒ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጊኒ አየር መንገድን እንዲያቋቁም ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱን የማቋቋሙ ሂደት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል። አገራቱ አየር መንገዱን ለማቋቋም ያደረጉት ስምምነት አፍሪካን ወደ አንድ ለማምጣትና የበለጠ ለማቀራረብ  ከማስቻል በላይ የኢትዮጵያንና ጊኒን ሁለትዮሽ ግንኙነትንም ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል። የኢኳቶሪያል ጊኒ ርዕሰ መዲና ማላቦ አየር መንገዱ በአፍሪካ ካሉት የመዳረሻ ከተሞች አንዷ ናት። አቶ ተወልደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ባላት የነዳጅ ሀብት "የአፍሪካ ኩዌት" በማለት የገለጿት ሲሆን አገሪቷ አየር መንገድ ለማቋቋም ፈተና ሆኖባት እንደነበር አውስተዋል። ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገሪቷ ፕሬዚዳንት ቲኦዶር ኦቢያንግ በቀረበ ጥያቄ መሰረት አየር መንገዱን የማቋቋምና የማስተዳደር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ባለቤትነቱ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የሆነው የአገሪቷ ብሔራዊ አየር መንገድ ከእ.አ.አ 2011 ጀምሮ በሚያከናውነው ስራ ትርፍ እያገኘ ባለመሆኑ ምክንያት የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በህዳር ወር 2012 ዓ.ም የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑናቸውን ገልፀዋል። አየር መንገዱ ካለው ድርሻ ኢትዮጵያ አየር መንገድን እንዲገዛ ጥያቄ ካቀረበ አየር መንገዱ በጉዳዩ ላይ እንደሚያስብበት ገልጸው ነበር። እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ አየር መንገዱ ያለው ፍላጎት የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ወደቀድሞው ዝናው እንዲመለስ ነው። ናይጄሪያና ቶጎ ጎረቤት አገሮች ሲሆኑ በአውሮፕላን በረራ ከአንዱ አገር ወደ ሌላኛው አገር ለመሄድ የሚጀፈው 45 ደቂቃ ነው። በሁለቱ አገራት መካከል የአየር በረራ ባለመኖሩ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር ለመሄድ በረራዎች የሚካሄዱት በለንደን በኩል መሆኑን ጠቅሰው ይህም የሰባት ሰአት የበረራ ጊዜ እንደሚፈጅ አቶ ተወልደ ይገልጻሉ። አየር መንገዱ በቶጎ ሎሜ የስካይ አየር መንገድ ስራ በማስጀመሩ ሰባት ሰዓት የሚወስደውን የአየር በረራ ጊዜ እንዳስቀረው አመልክተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ እያከናወነ ያለው ስራ ሁሉም የአፍሪካ አየር መንገዶች የሚመኙት ዓይነት እንደሆነና ለአህጉሪቷም ትልቅ መነሳሳት የፈጠረ ነው ብለዋል። አየር መንገዱ በአሁኑ ሰአት የቻድ፣ ቶጎ፣ ማላዊ እና ሞዛምቢክ አየር መንገዶችን እያስተዳደረ ይገኛል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ120 በላይ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፤በኢትዮጵያ ደግሞ  መዳረሻዎቹ 22 ናቸው። እ.አ.አ በ2019 አየር መንገዱ 12 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን ማጓጓዙም ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም