ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሐ ግበር ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ-የግብርና ሚኒስቴር

ኢዜአ ጥር 5 / 2012..በኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመታት በሚካሄደው የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሐ ግብር ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ መርዓ ግብር ላይ  ያዘጋጀው ውይይት በባህር ዳር ተደርጓል። በሚኒስቴሩ የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዋነኛው የወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በዚህም ወጣቶችን በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሰብል ልማት፣ በተፈጥሮ ሃብት፣ በእንስሳት ሃብት ልማት፣ በመኖ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ለማሰማራት መታቀዱን ገልጸዋል። በአገሪቱ ከሚለማው 36 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን የለማው 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑ በቀጣይ ወጣቶቹን ለማሰማራት ያስችላል ብለዋል። በተጨማሪም መንግሥት ለሥራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ ብድር በማመቻቸት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ አቶ ስለሺ ተናግረዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራ ግብረ ኃይል በማጠናከር የአመለካከት ውስንነት፣ የገበያ ችግር፣ የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት፣ የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው በክልሉ  ሥራ አጥነት፣ የስራ ማስጀመሪያ ካፒታልና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት እጥረት  ችግሮች እንደሚታዩ ገልጸዋል። ሥራ ፈላጊው ወጣት ዘንድ ሰርቶ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን ለመጥቀም የሚያስችል አስተሳሰብ  አለማዳበሩና የሥራ ተነሳሽነት ማጣት እንደሚታዩ  ጠቅሰዋል። ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመለወጥም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘመናዊ አሰራርና ክህሎት ላይ የተመሰረተ ስልጠና በተከታታይ ይሰጣል ብለዋል። ኅብረተሰቡ የሥራ ዕድል ፈጠራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ሊረባረብበት ይገባል ያሉት ደግሞ የፓናሉ ተሳታፊ አቶ ንዋይ አልታሰብ ናቸው። በገጠር በሚጠበቀው ልክ ሥራ መፍጠር ካልተቻለ ወጣቶች ወደ ከተሞች እያደረጉት ባለው ፍልሰት ሥራ አጥነት መጨመሩን ተናግረዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶችና ኅብረተሰቡ የገጠር ማዕከላት አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት  እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል። ከፌዴራልና ከክልሎች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ኢንተርፕራይዞችና እንግዶች ውይይቱ በጋራ ለመስራት ተነሳሽነት እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በአገር ደረጃ መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ከ2008 ወዲህ በግብርናው ዘርፍ ብቻ ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ ሥራ መፍጠሩ ተወስቷል። “የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ለአገር ብልፅግና!” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው አገር አቀፍ የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ የኤግዚቢሽንና የባዛር ዝግጅቶች ነበሩት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም