ፓርቲው የአገሪቱ ሕዝቦች በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የዜጋ ፖለቲካ ሥርዓት ለማስፈን እሰራለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው የአገሪቱ ሕዝቦች በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የዜጋ ፖለቲካ ሥርዓት ለማስፈን እሰራለሁ አለ
ኢዜአ፤(ሰቆጣ) ጥር 5 /2012 የአገሪቱ ሕዝቦች በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የዜጋ ፖለቲካ ሥርዓት ለማስፈን እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ/ኢዜማ/ አስታወቀ። ፓርቲው በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል። የኢዜማ አባል አቶ ወንደወሰን ተሸመ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ፓርቲው ማህበራዊ ፍትህን ለዜጎች በእኩልነት ለማንገስ ይሰራል። ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የፌዴራል ሥርዓት ለመገንባት እንደሚሰራም ተናግረዋል። "ብሄር ላይ ብቻ የተመሰረተ ፖለቲካን መከተል አገር ለመከፋፈልና እርስ በርስ ለመነቋቋር ዳርጎናል" ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ ከችግሩ ለመውጣት የፓርቲውን የፖለቲካ መስመር መከተል ወሳኝ ነው ብለዋል። በመሆኑም ሁሉም የአገሪቱ ብሄሮች/ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነትና በፍትሃዊነት በኢኮኖሚው ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚጥር አስታውቀዋል። ፓርቲው በወረዳዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በመክፈትና መሰል የውይይት መድረኮችን በማካሄድ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በውይይት መድረኩ የኢዜማ አባላት፣ ደጋፊዎችና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።