የደህንነት ቀበቶን በመጠቀም አደጋን መቀነስ እንደሚገባ አሽከርካሪዎች ተናገሩ

ኢዜአ ጥር 4/2012 በተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠመው የደህንነት ቀበቶን በመጠቀም አደጋን መቀነስ እንዲቻል እያንዳንዱ ሰው አዲስ የወጣውን መመሪያ ሊተገብረው እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡ የደህንነት ቀበቶን አሽከርካሪው እና ተሳፋሪዎቹ የመጠቀም ሕግ ከጥር 1 ቀን 2012  ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር አሽከርካሪዎችንና  ተገልጋዮችን አነጋግሯል፡፡ በመመሪያው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሸገር የከተማ አውቶብስ አሽከርካሪ አቶ ሞገስ ጋሻው፤ “የደህንነት ቀበቶ መጀመሪያ የተሰራውና በመኪኖች ላይ የተገጠመው አደጋን ለመከላከል ነው” ይላሉ፡፡ ″እኔ የደህንነት ቀበቶ ማሰር የጀመርኩት ማሽከርከር ከጀመርኩበት ከ1994 ጀምሮ ነው″ያሉት አቶ ሞገስ፤ የወጣው መመሪያ አስገዳጅ በመሆኑ ቀበቶውን የማድረግ ግዴታ አለብን ብለዋል፡፡ አቶ ሞገስ በሰጡት አስተያየት የደህንነት ቀበቶን ጠቀሜታ በአግባቡ ባለመረዳት ″በእኛ ሀገር ብዙውን ጊዜ መኪና ሲያሽከረክሩ ቀበቶ ማሰር  ጉረኛ″ የሚያስብልበት አጋጣሚ  መኖሩ ጠቀሜታው እንዳይጎላ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ የተሽከርካሪ የደህንነት ቀበቶን የመጠቀም አስገዳጅ ሁኔታ ከሹፌሩ በተጨማሪ  የተሳፋሪም ጭምር ሆኖ ህጉ ወደተግባር መግባቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በሰው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ  አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል፡፡ የደህንነት ቀበቶን ማሰር ከሚከሰት የትራፊክ አደጋ የመትረፍ መጠን የጎላ መሆኑን በመረዳት ተጠቃሚው በራሱ ፍላጎት መጠቀም እንደሚገባው የተናገሩት አቶ ሞገስ፤ የትራፊክ ፖሊሶችና የትራንስፖርት ባለስልጣን ባለሙያዎች ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ የደህንነት ቀበቶዎቹ  “አሽከርካሪው  በፍጥነት በማሽከርከር ላይ ባለበት ወቅት ድንገት ፍሬን ቢይዝ፣ ከመኪና መጋጨትና መገልበጥ አደጋ ቢያጋጥም “ እስከ 50 በመቶ  በሰው ላይ የሚደረስ ጉዳትን የመቀነስ ጠቀሜታ እንዳለው  የመንጃ ፍቃድ ስልጠና ላይ በነበሩበት ወቅት ግንዛቤ ማግኘታቸውን የሚገልጹት ደግሞ የታክሲ አሽከርካሪ  አቶ ሳሙኤል ሀብታሙ ናቸው፡፡ አቶ ሳሙኤል አሁን በታክሲ  ላይ ሹፌር ሆነው እየሰሩ ቢሆንም፤ የደህንነት ቀበቶ  ያላቸው ታክሲዎች በከተማው ውስን  በመሆናቸውና የሚሰረቅ በመሆኑ  መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ከሱሉልታ አዲስ አበባ በየእለቱ በትራንስፖርት እየተመላለሱ ስራ እንደሚሰሩ  የገለጹት አቶ ሀይሉ ፈይሳ በበኩላቸው  መንግስት ተሽከርካሪዎች የደህንነት ቀበቶ  መጠቀምን  የሚያጠናክር ህግ ማውጣቱን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ የደህንነት ቀበቶ  ከስሙ እንደሚንረዳው  ደህንነት መጠበቂያ መሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ  ቀበቶውን አስሮ በተሽከርካሪ መጓዝ በድንገት ከሚከሰቱ አደጋዎች የመቀነስ ጥቅም አለው ብለው እንደሚቀበሉት አስረድተዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን የትራፊክ  አደጋ ለመከላከል  ሁሉም ተባብሮ ለመፍትሄው መስራት  ይገባል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም