ምዕመናን የሰላም ምሳሌ በመሆን የኢትዮጵያን ሰላም እንዲያስጠብቁ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ምዕመናን የሰላም ምሳሌ በመሆን የኢትዮጵያን ሰላም እንዲያስጠብቁ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ
ኢዜአ፤ ጥር 4/2012 ምዕመናን የሰላም ምሳሌና አምባሳደር ሆነው የኢትዮጵያን ሰላም እንዲያስጠብቁና ለዘመናት የቆየውን አብሮነት እንዲያስቀጥሉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
የሰላም ሚኒስቴር በበኩሉ የሃይማኖት ጠንካራ አስተምህሮና ለዘመናት የቆየ የአብሮነት ባህል ኢትዮጵያን በሰላምና ፍቅር ማሻገሩን በመግለጽ፤ አሁን እየታየ ያለው የሰላም እጦት ችግር የተከሰተበትን ምክንያት የሃይማኖት አባቶች መመርመር እንዳለባቸው አመልክቷል።
የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ''ሃይማኖቶች ለሰላም'' በሚል መሪ ሃሳብ የግማሽ ቀን የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙ አባቶች የአንዱ ሃይማኖት ተከታይ የሌላውን እየገነባ መምጣቱንና በዘመናቻውም ያስተዋሉት ይህንኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃትና የሚደርሰው ጉዳት ለአገሪቱ መድሃኒት ሳይሆን ጥፋት እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ገልጸዋል።
''የሚያውኩን ጥቂቶች የምንታወከው ግን ብዙዎች ነን'' ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ''ጊዜ ያመጣው ችግር ሲገጥም ወቅቱን ጠብቆ ማለፉ አይቀርምና ምላሽ መስጠት ተገቢ አይደለም'' ብለዋል።
መጥፎ ነገር መስራት ለነገ ማስቀመጥ በመሆኑ ለአገርና ለህዝብ በማሰብ የመጣውን መከራ በትዕግስት በማለፍ አንድነትን ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ተወካይ አባ ዶክተር ኃይለገብርኤል መላኩ በበኩላቸው ''የሰላም ጉዳይ ትኩረትን ያሻል፤ ሰላም በመላ አገሪቱ እንዲሰፍን የሰላም ሚኒስቴር ሊሰራ ይገባል፤ የሃይማኖት ተቋማትም መፀለይና ማስተማር አለባቸው'' ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲዎችና በሃይማኖት ተቋማት ጥቃት ማድረስና ተማሪዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረግ ሃጥያት መሆኑን ገልጸው፤ ቤተክርስቲያኗ የምትቃወመው ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስትያናት ኀብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዱ ሰዎች ከጥቃት ይከለሉባቸው የነበሩ የሃይማኖት ተቋማት እየተደፈሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
''በሃይማኖት ተቋማትም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች ጥቃቶች ሲደርሱ ሁሉም ያገባኛል ሊል ይገባል'' ብለዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው በአገሪቱ ያሉ ሃይማኖቶች ለዘመናት በመከባበርና በሰላም አብረው መኖር የቻሉበት ዋነኛ ምክንያት ከሃይማኖት አስተምህሮ እንደሚሆን ሚገነዘቡ መሆኑን ተናግረዋል።
የየሃይማኖቱ ጠንካራ አስተምህሮና ለዘመናት የዳበረው የአብሮነት ባህል ኢትዮጵያውያን በሰላምና በፍቅር ዘመናትን እንዲሻገሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ይህ አስተምህሮ አሁንም ሊጠበቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በፅኑ እንደሚያምኑ ነው የገለፁት።
አሁን ላይ ከወትሮ በተለየ መልኩ ህዝቡ አንድነቱን እንዲጠብቅና በሰላም ወጥቶ እንዲገባ አንድነትን ከሚጎዳ ሃሳብ በተፃራሪ እንዲቆም ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አሁን ላይ እየተከሰተ ያለው የሰላም እጦት ችግር መንስዔ ምን እንደሆነ ሊመረምሩ እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።