ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ከፋይናንስ ቀውስ ለማዳን ተቋማት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት ሊመሩ ይገባል

ኢዜአ ጥር 4/2012.. ኢትዮጵያን ከፋይናንስ ቀውስ ለመታደግ ሁሉም ተቋማት 'ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን' ስርዓት ሊተገብሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አሳሰበ። የኢትዮጵ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ጋር በመተባበር 'አይ ኤፍ አር ኤስ' ወይም "ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ" ስርዓት ዙሪያ ከአገር አቀፍና የክልል የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተካሂዶ ነበር። ኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ160 በላይ አገሮች ተግባራዊ እያደረጉት ያለውን 'ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ" ስርዓት በ2007 ዓ.ም በአዋጅ አፅድቃ ወደ ትግበራ ገብታለች። አዋጁን ለማስፈጸምና ዘርፉን ለመምራት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂክመት አብደላ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በርካታ አገሮች በአዲሱ የፋይናንስ ስርዓት በመጠቀም ውጤታማ ሆነዋል። ስርዓቱ አገሮች በራሳቸው የፋይናንስ አቀራረብ ስርዓት ሲመሩ በነበረበት ወቅት ያጋጥም የነበረውን ያለመናበብ ችግር መፍታቱን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ይህን ስርዓት መተግበሯ የራሷን የሂሳብ አሰራር ለመፍጠር የሚወስደውን ወጭ መታደጉን ጠቅሰዋል። ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ተቋማትና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ተቀብሎ መተግበር ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት፣ ተቋማት ከኪሳራና ውድቀት ማዳን፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት ማስፈን፣ የአገር ኢኮኖሚን ማጠናከር፣ ፍትሀዊ የንግድ ፉክክር እንዲጎለብት ከማድረግና የህዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። ስርዓቱ በድርጅቶች ግልፅነትና ተጠያቂነት ስለሚያሰፍን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊገጥማት ከሚችለው የፋይናንስ ቀውስ ለመታደግ 'የዓለም አገሮች የፋይናንስ ቋንቋ' እየሆነ የመጣውን አይ ኤፍ አር ኤስ /IFRS/ በሁሉም የመንግስት፣ የግልና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ሂክመት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የህግና የህግ ማስከበር ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ ተቋሙ በአሰራሩ ግንዛቤ እንዲፈጠር በሚዲያ የማስተዋወቅ፣ ስልጠና የመስጠትና የሂሳብ የሙያ ማህበራትን የማቋቋም ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው ተቋማት ሪፖርታቸውን በዚህ ስርዓት አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ መደረጉን ገልፀዋል። ለአብነትም የፋይናንስ ተቋማትና መንግስታዊ የልማት ድርጅቶች ዓመታዊ ሪፖርታቸውን በዚህ አሰራር ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በህጋዊነት የተቋቋሙ ማንኛውም ድርጅቶች አዋጁ እንደሚመለከታቸው ገልጸው፤ የሂሳብ አሰራር ስርዓቱን ተግባራዊነት ትክክለኛ ደረጃዎችን ማካተቱን መረጋገጥ እንዳለበት ጠቁመዋል። ''አሰራሩ ለፋይናንስ ድርጅትችም ሆነ ከፋይናንስ ቀውስ ለመዳን ያግዛል'' ብለዋል። በፋይናንስ ቀውስ የተነሳ በርካታ አገሮች ብድር መመለስ ተስኗቸው መሰረተ ልማቶቻቸውን ለአበዳሪዎች አሳልፈው እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ የውጭ ብድር ያለባቸው አገሮች የሂሳብ አያያዝ ስርዓት መተግበር እንደሚያስፈልጋቸውም አስረድተዋል። ተበድሮ መስራት ተገቢ ቢሆንም የመክፈል አቅምን ያገናዘበ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል። ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ስርዓት ለመተግበር በዘርፉ የሰለጠነ ብቁና በቂ የሰው ሃይል እጥረት መኖሩን ሃላፊዎቹ ገልጸዋል። በዚህም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በቂና ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት መታቀዱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም