የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አቶ ፍትህ ወልደሰንበትን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አቶ ፍትህ ወልደሰንበትን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ
ኢዜአ ጥር 4/2012 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ አቶ ፍትህ ወልደ ሰንበትን መረጠ። ፌዴሬሽኑ ትናንት በአዲስ አበባ 19ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል። ጠቅላላ ጉባዔው ለቀጣይ አራት አመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩ አምስት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አድርጓል። ላለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን ሲመሩ የቆዩት አቶ ፍትህ ወልደ ሰንበት በድጋሚ ፕሬዝዳንት ሆነው በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠዋል። ጠቅላላ ጉባዔው በ2011 ዓ.ም. የፌዴሬሽኑን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም በ2012 ዓ.ም መሪ ዕቅድ እና ሌሎች አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት አድርጎባቸዋል። በውይይቱ የክለቦች ቁጥር እንዲጨምር መደረጉ፣ በአህጉር አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ፣ የሴቶች ሻምፒዮና ራሱን ችሎ መካሄዱ በጥንካሬ ተነስቷል። በተጨማሪም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸው እንዲሁም በግንኙነቱ አቶ ፍትህ የምስራቅ አፍሪካ እጅ ኳስ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የውድድር ኮሚሽነር ሆነው መመረጣቸው በጉባዔው በመልካም ጎን ተጠቅሷል። በሌላ በኩል የዳኞች እና የአሰልጣኞች ብቃት ማሳደግ፣ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እንዲጀመር እና የክለቦች ቁጥር እንዲጨምር ፌዴሬሽኑ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ጉባዔው አሳስቧል። በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 2020 በሚካሄደው የዞን አምስት ቻሌንጅ ትሮፊ ውድድር በብቃት ለማስተናገድ እና ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ጉባዔው አቅጣጫ አስቀምጧል። የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌደሬሽን ተወካይ ዑጋንዳዊቷ ሚስ ሼይላ ሪቻርድሰን በጉባዔው ላይ ተገኝተው ምርጫውን እና የጉባዔውን ሂደት መታዘባቸውን ከስፖርት ኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።