የ52 ዓመቱ አንጋፋው እግር ኳስ ተጫዋች ካዙዮሺ ሚውራ ለተጨማሪ አንድ አመት ሊጫወት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ52 ዓመቱ አንጋፋው እግር ኳስ ተጫዋች ካዙዮሺ ሚውራ ለተጨማሪ አንድ አመት ሊጫወት ነው
ኢዜአ፤ጥር 4/2012 የዓለማችን አንጋፋ የሆነውና 52 ዓመት እድሜ ላይ የሚገኘው የእግር ኳስ ተጫዋች ካዙዮሺ ሚውራ አሁንም ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመጫወት ከክለቡ ዮካሃማ ኤፍሲ ጋር የኮንትራት ስምምነት ተፈራርሟል። የእግር ኳስ ጨዋታ የአጭር ጊዜ የስራ ቆይታ የሚደረግበት ሙያ በሚል በእግር ኳሱ ባለሙያዎች ይገለፃል። እስካሁን ባለው ልምድ መሰረትም 15 ዓመት በአማካይ ተጫዋቾች በእግር ኳስ የሚቆዩበት ጊዜ ነው። ካዙዮሺ ሚውራ ግን ባልተለመደ ሁኔታ የእግር ኳስ ባለሙያዎችን ግምትና ትንበያ በተቃረነ መንገድ ለ35 ዓመት እግር ኳስን የተጫወተ ስፖርተኛ ሆኗል። ጃፓናዊ የአጥቂ መስመር ተጨዋች በጃፓን ጄ ዋን ሊግ ለሚጫወትበት ዮካሃማ ኤፍሲ ጋር ያለውን ኮንትራት በአንድ ዓመት አራዝሟል። በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም 53 ዓመቱን የሚይዘው ካይዙሺ ሚውራ የኮንትራት ስምምነነቱን ተከትሎ ለ35ኛ የውድድር ዓመት እግር ኳስን መጫወቱን እንደሚቀጥል የጀርመኑ ዶይቼ ቬሌ በድረ ገጹ አስፍሯል። እ.አ.አ በ1967 በጃፓን ሺዞካ ከተማ የተወለደው ካይዙሺ ሚውራ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው እ.አ.አ በ1986 በብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ ነበር። አሁን ያለበትን ዮካሃማ ኤፍሲን ጨምሮ ካይዙሺ ለ14 ክለቦች ተጫውቷል። ካይዙሺ ሚውራ እ.አ.አ ከ1990 እስከ 2000 ለጃፓን ብሔራዊ ቡድን 89 ጨዋታዎችን አድርጎ 55 ግቦችን በማስቆጠር 80 ግብ ካስቆጠረው ኩኒሺጌ ካማሞቶ በመቀጠል የብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው። አሁንም ለተጨማሪ አንድ ዓመት መጫወቱ የአጥቂውን የአካል ብቃት የአዕምሮ ዝግጁነት አስገራሚ እንደሚያደርገው ነው የዶይቼ ቬሌ ዘገባ የሚያመላክተው። በየዓመቱ የዓለም ድንቃ ድንቅ ታሪኮችን የሚያወጣው "ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ" እ.አ.አ በ2018 ካይዙሺ ሚውራን አንጋፋው የእግር ኳስ ተጫዋችና በእግር ኳስ በእድሜ ትልቁ ግብ አስቆጣሪ በሚል እውቅና ተሰጥቶታል። ካይዙሺ ሚውራ እ.አ.አ በጃፓኑ ክለብ ዮካሃማ ኤፍሲ በ51 ዓመት በመጫወትና ግብ በማስቆጠር ነው በ"ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ" እውቅ ናሊያገኝ የቻለው።