ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ በዋሺንግተን ዲሲ ይወያያሉ

ኢዜአ፤ ጥር 4/2012 የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ውይይት ያደርጋሉ። ሶስቱ አገራት በደረሱት ስምምነት መሰረት ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ የመጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ማካሄዳቸው ይታወሳል። በውይይቱ ለመሳተፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ትናንት ዋሺንግተን ዲሲ መግባታቸው ገብተዋል። ሁለተኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል። ታህሳስ 29 እና 30 ቀን 2012 ዓ.ም የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ በግድቡ ዙሪያ ያካሄዱት አራተኛና የመጨረሻው የቴክኒክ ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ ግብጽ ያቀረበችው አዲስ ሀሳብ ውይይቱ ያለውጤት እንዲጠናቀቅ ምክንያት መሆኑን ገልጸው ነበር። በዛሬው ውይይት ላይ በአራቱ ተከታታይ የቴክኒክ ስብሰባዎች ዙሪያ ገለጻ እንደሚደረግም ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም