በጋምቤላ የቱሪዝም ዘርፉን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር አለበት---አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ የቱሪዝም ዘርፉን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር አለበት---አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ኢዜአ ጥር 3/2012 ፡- በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የቱሪዝም መስህብ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ፡፡ የአለም የቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለተሻለ ህይወት “ በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል፡፡ በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት በክልሉ ያለውን ሰፊ የቱሪዝም መስህብ ሀብት በአግባቡ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ እንዲውል ዘርፉን ማሳደግ ይገባል፡፡ ዘርፉ ለወጣቱ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በክልሉ ባለፉት ዘመናት የተከናወኑ ታሪካዊ ክስተቶችንና ተፈጥሯዊ ገጽታዎችን በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በተለይም ዘርፉ ክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን በጎ ገጽታ ለውጪ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ሰፊ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች ቢኖሩም ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም አነስተኛ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቁመዋል፡፡ መንግስት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ከመስኩ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረው ለዚህም ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብና ለሌሎች የማስተዋወቅ ፣ ሆቴሎችና አስጎብኚዎችም አገልግሎታቸውን በማጠናከር ለዘርፉ እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አሪያት ኡጁሉ በበኩላቸው ቢሮው በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፋራዎችን ለማስተዋወቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የዱር እንስሳትና ኢኮ-ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ጋር በመሆን በክልሉ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በቱሪዝም ቀን አከባበር ስነሰርዓት ከተሳተፉት መካከል አቶ ኡቦንግ ኜየል እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። በተለይ መንግስት የቱሪስት መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የመንገድ መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት አንስቶ የሰለጠነ የሰው ኃይል ዘርፉን እንዲመራው ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ በአለም የ” ባዮስፌር ሪዘርቭ” የተመዘገበውን የማጃንግ ጥቅጥቅ ደንን ጨምሮ ሌሎች ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቢኖሩም ዘርፉ ግን እንደ ሀገር አቀፍ ደረጃም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ቲቶ ሐዋሪያት ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የአንድ ቢሮ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲው የዱር እንስሳትና ኢኮ-ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ሰለሞን ቶማስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንዳመለከቱት በክልሉ ሰፊ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦች ቢኖሩም የመሰረተ ልማት አውታሮች ባለመዘርጋታቸው ዘርፉ የተፈለገውን ጥቅም ማስገኘት አልቻለም፡፡ በተለይም የመንገድ አለመሟላት፡የሆቴሎች አለመስፋፋት፣ በዘርፉ የተሰማሩ አስጎብኚዎች አለመኖር፡ የማስተዋወቅ ስራ ክፍተት እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ዘርፉ ለክልሉ ሊያበረክት የሚችለውን ጥቅም ማሳጣቱን ጠቁመው በቀጣይ ዘርፉን ለማሳደግ በተለይም ወጣቶችን በማሳተፍ የተቀናጀጀ ስራ ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡