በደምቢ ዶሎ ከታገቱ ተማሪዎች መካከል 21 መለቀቃቸው ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በደምቢ ዶሎ ከታገቱ ተማሪዎች መካከል 21 መለቀቃቸው ተገለፀ
ኢዜአ፤ ጥር 2/2012 ታግተው የነበሩ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ከታገቱት ተማሪዎች ውስጥ 13 ሴትና 8 ወንድ በድምሩ 21 ተማሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ መለቀቃቸውን ያስታወቁት አቶ ንጉሱ፤ አሁንም ቀሪ 6 ተማሪዎች በእገታ ላይ መሆናቸውን በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል መረጃ መስጠቱን ተናግረዋል።
አቶ ንጉሱ እንዳብራሩት ሰሞኑን በደምቢ ዶሎ ብቻ ሳይሆን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 16 ዩኒቨርሲቲዎች የፀጥታ ችግሮች እንደነበረና በዚህም ወደ 35 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ወደየቤታቸውና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎቹን ለቀው ሄደዋል። በነዚህ ዩኒቨርሲቲዎ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ከቦርድ አመራሮች እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም ያነሱት አቶ ንጉሱ፤ ከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲዎችን የማረጋጋት ስራ የሚሰራ ቡድን መዋቀሩን እንዲሁም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ማስከበር ስራ እንዲሰራ ትእዛዝ ተላልፎ እየተሰራ መሆኑን ልጸዋል። የአመራር ችግር ባለባቸው ዩኒቨርሲቲዎችም የማስተካከያ ስራ መሰራቱን እና ከችግሮቹ ጋር ተያይዞ ጥፋተኛ የሆኑ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አንስተዋል። ችግር ከተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ሲከሰት በስጋት ከጊቢ ወጥተው ጉዞ ላይ ያሉ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ መታገታቸውን ነው ያነሱት። የታገቱ ተማሪዎችን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በማንም ላይ ጉዳት ሳይደርስ ማስለቀቅ ተገቢ በመሆኑ እና የመንግስትም ቀዳሚ ስራ በመሆኑ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአካባቢው ወጣቶች፣ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከሌሎች የፀጥታ መዋቅር ጋር ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። እስካሁን ታግተው ያሉትን በሰላማዊ ሁኔታ ለማስለቀቅ እና ልጆቹ ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዲወጡ ለማድረግ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች በአካባቢው ወግና ባህል መሰረት እንዲሁም በፀጥታ አካላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ አካላት በቁጥርም የተለያዩ መረጃዎችን እየሰጡ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ በአካባቢው መንግስት ያሰማራው የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የአካባቢው የፀጥታ መዋቅር በጋራ የገመገመው እስካሁን አንድ የአካባቢውን ወጣት ተማሪ ጨምሮ 6 ተማሪዎች እንደታገቱ ናቸው ብለዋል። ቀሪዎቹን ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለማስለቀቅ፤ መንግስትም የአካባቢው ህብረተሰብም እየሰሩ መሆኑን ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ አስፈላጊውን መረጃ በየጊዜው ለህብረተሰቡ እንደሚያደርሱም ተናግረዋል፡፡