የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ አቻው 2 ለ 0 ተሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ አቻው 2 ለ 0 ተሸነፈ
ኢዜአ ጥር 2/2012... የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የቅድመ-ማጣሪያ ጨዋታ በዩጋንዳ አቻው 2 ለ 0 ተሸነፈ። 7ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት 2013 ዓ.ም በህንድ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ የሚደረጉ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ትናንት መካሄድ ጀምረዋል። ዛሬ በካምፓላ ስታር ታይምስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የዩጋንዳ ከ17 ዓመት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን 2 ለ 0 አሸንፏል። ጁሊየት ናሉኬንጌ በ6ኛው ደቂቃ ካትሪን ናጋድያ በ87ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም ይደረጋል። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመልሱ ጨዋታ በሶስት ግብ ልዩነት ካሸነፉ ከቅድመ ማጣሪያ ወደመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ያልፋሉ። ዛሬ የተመዘገበው ውጤት በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድን ውጤቱን ቀልብሶ ወደቀጣዩ ዙር የማለፍ የቤት ስራውን በጣም ከባድ አድርጎታል። ትናንት በአፍሪካ ዞን በተደረጉ የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የቅድመ-ማጣሪያ ጨዋታዎች ሞሮኮ ጅቡቲን 7 ለ 0፤ ቦትስዋና ዚምባቡዌን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈዋል። የቅድመ-ማጣሪያ የመልስ ጨዋታዎች በቀጣይ ሳምንት የሚደረጉ ይሆናል። አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን የማሳተፍ ኮታ አላት። በህንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 7ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።