የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጀምሯል
ኢዜአ ጥር 2/2012 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል። በሁለቱም ጾታዎች በሚካሄደው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር በሴት ስድስት በወንድ አምስት ክለቦች ይሳተፋሉ። ጎንደር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን፣ ሀዋሳ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ እና አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ጅማ ከተማ በሴቶቹ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው። ሀዋሳ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ጎንደር ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማና አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮ በወንዶች ይሳተፋሉ። በዚሁ መሰረት በሀዋሳ በወንዶች የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ሀዋሳ ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 74 ለ57 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል። ነገ በሴቶች ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ፤ ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ከአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ጋር እንዲሁም በወንዶች ነገ ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ነገር ግን ክለቦቹ በበጀት ጉዳይ ላይ ያልጨረስናቸው ጉዳዮች አሉ ጨዋታዎቹ ሌላ ጊዜ ይራዘሙልን በሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ጥያቄውም አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ ጨዋታዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘማቸውን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ የውድድር ዓመት ነው። ሀዋሳ ከተማ በወንዶች ጎንደር ከተማ በሴቶች የባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው። በሌላ የስፖርት ዜና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ሰበታ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 3 ለ 1 አሸንፏል። ለሰበታ ከተማ ፍጹም ገብረማርያም በፍጹም ቅጣት ምት፣ መስዑድ መሐመድና ቡርኪናፋሶዋዊው ሲይላ ዓሊ ባድራ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ጋናዊው አጥቂ ያኩቡ መሐመድ ለጅማ አባ ጅፋር ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። የፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ነገ በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች ቀጥለው የሚካሄዱ ይሆናል።