ቀጥታ፡

በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው 'ሶደሬ ሪዞርት' ሆቴል ተመረቀ

ኢዜአ ጥር 2/2012.. በአዲስ አበባ ከተማ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው 'ሶደሬ ሪዞርት' ሆቴል ዛሬ ተመረቀ። አፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ፊት ለፊት የተገነባው ሆቴሉ 50 ያህል አልጋዎች ያሉት ሲሆን አሁን ላይ 75 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ ተገልጿል። የሆቴሉ ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ከተመረቀው ሆቴል በተጨማሪ በአዲስ አበባ አዲሱ ገበያ አካባቢ ሌላ ሆቴል በማስገንባት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ግንባታው በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማና ቢሾፍቱ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ ተጨማሪ ሆቴሎችን በመስራት ደረጃውን የጠበቀ አግልግሎት ለመስጠት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አመልክተዋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በእንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ በከተማዋ የሆቴል ግንባታ ስራ የቱሪዝሙ ዋና አጋዥ ኃይል ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ 10 ሺህ ያህል የሆቴል አልጋዎች ቢኖሩም ሁሉም ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም ሲሉም ገልፀዋል። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መገንባት ለከተማዋ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም