ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ለቱሪዝም ዕድገቱ መነቃቃትን ፈጥሯል-ምሁራንና አስጎብኚዎች

ኢዜአ ጥር 2/2012.. የኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ለቱሪዝም ዕድገቱ መነቃቃትን መፍጠሩን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና አስጎብኚዎች ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው ዘርፉን ለማሳደግ ለሰው ኃይል ልማትና ለጥናትና ምርምር ሥራዎችን ትኩረት መስጠቱን ገልጿል፡፡ ምሁራኑንና አስጎብኚዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት የአገሪቱ ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸው ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አሉበል ወርቄ የአገሪቱ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር የህዝቦቿን ማንነት ለማስተዋወቅ ያስችላሉ ብለዋል። ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በመገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቅ፣ የመዳረሻ ቦታዎችን ማልማትና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያቸው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመፍታት ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም በጎርጎራ አካባቢ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በመለየትና በአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ የሚታዩ ስጋቶችን መለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችንአመላክቷል ብለዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አስናቀው አዳነ በበኩላቸው በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶች ለቱሪዝም ዕድገት  ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን ይናገራሉ። ቅርሶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ መደረጉ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገለት ምዝገባ በቱሪዝም ዘርፍ ሀብት ለማፍራትና መነቃቃትን ለመፍጠር  እንደሚረዳ አቶ አስናቀው አስረድተዋል፡፡ በጎንደር ከተማና አካባቢዋ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አስጎብኚ አቶ ዳንኤል ፍርድያውቃል መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ የሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ነው፡፡ የጎብኚዎች ቁጥር የሚጨምረው ከታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎች በተጨማሪ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ ሆቴል ሲኖር ነው ያሉት ደግሞ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰሎሞን አወቀ ናቸው፡፡ የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ለዘርፉ ዕድገት አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ሆቴሎች ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዚህ ዓመት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ በልዩ ዝግጅት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም