ቀጥታ፡

የጋሞ አባቶች ግጭትን የማብረድ ባህላዊ እሴትን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ማስፋፋት ይገባል ተባለ

ኢዜአ ጥር 2/2012.. የጋሞ አባቶች ግጭትን ለማብረድ እየተጠቀሙበት ያለውን ባህላዊ ስርዓት ለትውልድ ለማስተላለፍና በመላው አገሪቱ ለማስፋፋት ምህራን በጥናትና ምርምር እንዲያግዙ ተጠየቀ። "የጋሞ አባቶች የሰላም ተምሳሌት ለአገር ግንባታ" በሚል የጋሞ ብሔረሰብ ባህልና ቋንቋ ሲፖሲየም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በዚሁ ጊዜ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ የጋሞ አባቶች እርጥብ ሳር በመያዝ ጸብንና ቁጣን የማብረድ ባህል ለዘመናት የኖረ እሴት መሆኑን አውስተዋል። እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘው የጋሞ ብሔረሰብ እንደሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭቶችን በባህላዊ መንገድ በመፍታት እርቅ ለመፍጠር የሚያስችል የቆየ ስርዓት ባለቤት ነው። በሰው ልጆች የእለት ተእለት ህይወት በሚኖር መስተጋብር ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በማብረድ የሚታወቀው ይህ ባህላዊ እሴት አሁንም ድረስ በጋሞ ህዝብ ዘንድ የቀጠለ መሆኑንም ጨምረዋል። ይህንን እሴት በጥናት በመደገፍና በመሰነድ ለአዲሱ ትውልድ ለማስተዋወቅ ብሎም ለሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም የእውቀት ምንጭ ሆኖ ያገለግል ዘንድ የሚደረገው ጥረት ግን አናሳ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል። በመሆኑም የጋሞ አባቶች ግጭትን ለማብረድ እየተጠቀሙበት ያለውን ባህላዊ ስርዓት ለትውልድ ለማስተላለፍና በመላው አገሪቱ ለማስፋፋት ምህራን በጥናትና ምርምር እንዲያግዙ ጠይቀዋል። የባህልና ቱሪዝም ሙያተኞችም እሴቱን ለቱሪዝም የገቢ ምንጭነት ማዋል የሚችሉበትን ሁኔታ ማጥናት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ በበኩላቸው የጋሞ አባቶች ችግር በመጣ ጊዜ ጉልበት ሳይሆን ትህትናን በማስቀደም "ተንበርክከው አሳይተውናል፣ ወጣቶችም ከነሱ እንማር" ብለዋል። ይህን ትልቅ ዋጋ ያለው እሴት መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የጋሞ ህዝብ የተለያዩ የጥበብ ባለቤት መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው ይህንን ባህል በቋሚነት የሚጎበኝበትና ለመላው ኢትዮጵያዊያን የእውቀቱ ምንጭነት እንዲውል ለማድረግ ራሱን የቻለ አንድ ማዕከል ለመገንባት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ገልፀዋል። በሲፖዚየሙ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጋሞ ዞን ተወላጆች፣ የህዝብ ተወካዮችም ምክር ቤት አባላትና ሌሎች የመንግስት አካላት ተገኝተዋል። በመርሃ ግብሩ የጋሞን ባህልና ቋንቋ የሚዳስስ ጹህፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚቀጥሉም ተገልጿል። የጋሞ አባቶች በ2011 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ሊከሰት የነበረውን ግጭት እርጥብ ሳር በመያዝና በመንበርከክ ማስቀረት የቻሉ ሲሆን ለዚህም በተለያዩ መድረኮች እውቅና እንደተሰጣቸው ይታወሳል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም