የወጣት ስራ አጥነት ችግርን በመቀነስ የወጣቶችን ወደግጭት የመግባት እድል መከላከል ይቻላል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የወጣት ስራ አጥነት ችግርን በመቀነስ የወጣቶችን ወደግጭት የመግባት እድል መከላከል ይቻላል ተባለ
ኢዜአ ጥር 2/2012 መንግስት የስራ አጥነት ችግር ን ለመቀነስ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር ወጣቱን ባለስራ ካደረገ የወጣቶችን ወደግጭት የመግባት እድል በመከላከል የአገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚቻል ተገለፀ። የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ "ለሰላም ዋጋ እንሰጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። በዓለም ላይ የስራ አጥነት ጉዳይ ለመንግስታት የራስ ምታት የሆነ ጉዳይ ሲሆን በተለይም የወጣት ስራ አጥነት ወጣቶች ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዲገቡና በአገራት ውስጥ ለሚነሱ ቀውሶች እንደ ምክንያትነት ይነሳል። እንደ ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት(አይኤልኦ) የ2019 ሪፖርት በዓለማችን ላይ ከ73 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ስራ አጥ እንደሆኑ ያመለክታል። በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተነስተው ለነበሩ ግጭቶች እንደ መንስኤ ከሚነሱት አንዱ የወጣቶች ስራ አጥነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንደነበርም ይታወቃል። በኢትዮጵያ የወጣቶች ስራ አጥነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣና መንግስትም ትኩረት ከሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል የወጣቶችና አጠቃላይ የስራ እድል ፈጠራ ማሳደግ ይገኝበታል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶችም መንግስት የወጣት ስራ አጥነት ላይ ትኩረቱን በማድረግ ወጣቶች ወደ ግጭትና ሁከት የሚገቡበትን ሁኔታ መፍትሔ የማበጀት ስራ መስራት እንዳለበት ይገልጻሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ተመራቂ ተማሪ ታደለው ዘመነ ተመራቂ ተማሪዎች ከዩንቨርስቲ ከወጡ በኋላ የስራ እድል እያገኙ ባለመሆናቸው በተለያዩ አካላት ግፊት ወደግጭትና ሌሎች እኩይ ተግባራት በቀላሉ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል ብሏል። ወጣቶች የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው በቀላሉ ወደግጭትና ሁከት ተግባር አይገቡም ያለው አስተያየት ሰጪው መንግስት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መርሃ ግብር አበክሮ መስራት እንዳለበት ተናግሯል። ለዘላቂ ሰላም መስፈን ከምንም በላይ መወያያት ወሳኝ እንደሆነና ተወያይቶ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባም ተማሪ ታደለው አክሎ ገልጿል። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጂኦግራፊካል ሳይንስና ኢንቫይሮመንታል ስተዲ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሚካኤል ከበደ ወጣቱ በስራ አጥነት ዙሪያ ያለውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንዳለበት ገልጿል። ወጣቱ ውስጣዊ ሰላሙ ላይ በቅድሚያ ትኩረት በማድረግ በምክንያታዊነት ላይ ተመስርቶ ሀሳቡን ማራመድ እንዳለበትም ተናግሯል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በቀለ ተቋማቸው በዘላቂ ሰላም ግንባታና ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ስራ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያድግ በዋንኛነት ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል። ስራ አጥነት ለሰላም መደፍረስ መንስኤ በመሆኑ ስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ሰላምን መፍጠር ላይ ያተኮረ ተቋማቸው ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ተቋሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል። በውይይቱ መድረኩ ላይ ሰላምን እንዴት ማምጣት ይቻላል? በሚል የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር የሥራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ማስታወቁ ይታወሳል። ለአብነትም ማስተር ካርድ ፍውንዴሽን እና የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ ኮሚሽን በጋራ በመሆን በመጪዎቹ አስር ዓመታት ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸው ይጠቀሳል። ይህ ፕሮጀክት 300 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን ቱሪዝም፣ ግብርና፣ አምራች እንዱስትሪዎች እና የአይ ሲ ቲ ዘርፍ ደግሞ የስራ ዕድሉ የሚፈጠርባቸው ናቸው፡፡