ቀጥታ፡

የሰሜን ሸዋ ዞን የደን ሽፋን 26 ከመቶ ደረሰ

ኢዜአ ጥር ዐ2/ 2ዐ12 በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የደን ሽፋን 26 ከመቶ መድረሱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ባለፈው ክረምት ከተተከሉ ችግኞች 1ዐ6 ሚሊዮን ችግኞች ጸድቀዋል። የጽህፈት ቤቱ የደን አያያዝና አጠባበቅ ቡድን መሪ አቶ ግርማ አሰፋ እንደገለጹት በዞኑ ከ10 ዓመታት በፊት ሁለት በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን 13 እጥፍ አድጓል። በዚህም በዞኑ 13 ወረዳዎች በሕዝብና በመንግሥት በተደረገው እንቅስቃሴ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ደን የተሸፈነው መሬት 258ሺ 697 ሄክታር ደርሷል ብለዋል። በተለይ ባለፉት 1ዐ ዓመታት በተደረገ የህዝብ ንቅናቄና ድጋፍ 156ሺ679 ሄክታር መሬት ተሸፍኗል።ደኑም ከአምስት ሜትር በላይ ከፍታ እንዳለው ቡድን መሪው ተናግረዋል። የዞኑ የተፈጥሮ ደን ሽፋን ከ102 ሺህ ሄክታር በላይ ሲሆን፣ ይህም በእምነት ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በጥብቅ የደን ስፍራዎች እንደሚገኝ አስረድተዋል። በዞኑ ከአንድ ወጥ የደን አጠቃቀምና አያያዝ መመሪያ በመተግበሩ የአካባቢው ሥነ ምህዳር ይዞታ መሻሻሉን አስታውቀዋል። በተለይ እርሻን ለማስፋፋት፣ ቤት ለመስራት ፣ የዱር እንስሳትን ለማባረርና ከሰል ለማክሰል ሲባል በሚፈፀም የደን ጭፍጨፋ የሚወድመው ደን መቀነሱን አብራርተዋል። የዞኑን የደን ሽፋን በአምስት ዓመታት ውስጥ 980 ሺህ 89ዐ ሄክታር መሬት ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል። ካለፈው ዓመት  ጀምሮ ስምንት የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ሠራተኞች በደን ልማት ተሰማርተው እንክብክቤ እያደረጉ መሆኑን አቶ ግርማ አመልክተዋል። የደን ሀብት የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ፣ በረሃማነት እንዳይስፋፋ ለመከላከል፣ የመሬት ለምነትና የአፈር ርጥበት ለማቆየት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። በዞኑ ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ ልማትና በመደበኛ መርሃ ግብር ከተተከሉ 133ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች መካከል ከ79 በመቶ በላይ የሚሆኑት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በቆጠራና በክትትል መረጋገጡን ቡድን መሪው አስታውቀዋል። በተመረጡና በተራቆቱ 9ሺ 271 ሄክታር መሬት ላይ የተተከሉት እነዚህ አገር በቀልና የውጪ ዝርያ ያላቸው የዛፍ ችግኞች በአብዛኛው የጸደቁት ኅብረተሰቡ አካባቢውን ከእንስሳትና ሰው ንክኪ በመከላከል፣ ችግኞቹን ውሃ በማጠጣት፣ በማረምና በመከታተል ባደረገው ድጋፍ መሆኑንም አረጋግጠዋል ። በዞኑ በልማቱ የተሳተፉት ተቋማት ባደረጉት ክብካቤና ድጋፍ አብዛኛዎቹ ችግኞች እንደፀደቁላቸውም አመልክተዋል። የዞኑ አርሶ አደሮች ማህበር ሊቀመንበር አቶ መከተ ደባልቄ  በበኩላቸው የደን ሀብቱ በአያያዝና አጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ ለጉዳት እንዳይዳረግ  በተቀናጀ መልክ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መርዕድ ኅብረተሰቡ የደን ሀብትን ለማልማትና ከህገወጥ ጭፍጨፋ ለመከላከል በተሰጠው ትምህርትና በልማትና ጥበቃ ሥራው በማሳተፍ ውጤት እንደተገኘበት ገልጸዋል። ''ችግኝ ተከላ የመጀመሪያ ደረጃ የደን ልማት አካል ነው'' ያሉት የደን ባለሙያ አቶ ስመኝ ደበሌ፣ ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመታት ድረስ ውሃ ማጠጣትን ጨምሮ እንክብካቤ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የደን ልማት 15 ከመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም